banner

በእስራኤል-አሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ሳቢያ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የ120 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ አስተናገደች

#FastMereja I መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም.

በእስራኤል-አሜሪካ እና በኢራን መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (UAE) ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ውድመት እያስከተለ ይገኛል። ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ብቻ በዱባይ እና በአቡ ዳቢ የአክሲዮን ገበያዎች ላይ የ120 ቢሊዮን ዶላር ሀብት ሲጠፋ፣ የሀገሪቱ የቱሪዝም፣ የአቪዬሽን እና የሪል ስቴት ዘርፎች ክፉኛ ተመተዋል።

እንደ Middle East Eye ዘገባ ከሆነ የዱባይ የአክሲዮን መረጃ ጠቋሚ (Index) ጦርነቱ ከጀመረበት የካቲት 21 ጀምሮ የ16 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። ይህ ውድቀት ከአቡዳቢ ገበያ ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ የከፋ ሆኖ ተመዝግቧል።

በጸጥታ ስጋት ምክንያት እስካሁን ከ18,400 በላይ በረራዎች ተሰርዘዋል። ይህም በዓለም አቀፍ የትራንዚት ማዕከልነቷ ለምትታወቀው ሀገር ትልቅ የገቢ ምንጭ መድረቅ ሆኗል።

እስከ መጋቢት 19 ቀን ድረስ ኢራን 398 ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን እና 1,872 ድሮኖችን ወደ ኤምሬትስ የተኮሰች ሲሆን፣ አብዛኞቹ ቢመከቱም የወደቁ ስባሪዎች በቡርጅ አል አረብ፣ በፓልም ጁሜይራ እና በፉጃይራ የነዳጅ ማከማቻዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

እንደ ሳውዲ አረቢያ እና ኦማን ያሉ ሀገራት በነዳጅ ዋጋ መናር ተጠቃሚ ቢሆኑም፣ በቱሪዝም እና በፋይናንስ ላይ የተመሰረተው የኤምሬትስ ሞዴል ለጦርነቱ ቀጥተኛ ተጋላጭ ሆኗል።

የሀገሪቱ መሪዎች የገበያ አዳራሾችን በመጎብኘት ህዝቡን ለማረጋጋት ቢሞክሩም፣ ተንታኞች ግን የደረሰው የኢኮኖሚ ጠባሳ በቀላሉ የሚሽር እንዳልሆነ እየገለጹ ይገኛል።

Leave a Comment