banner

170 የልብ ሕሙማን ሕፃናትን በ45 ቀናት ውስጥ ነፃ ሕክምና ለመስጠት ስምምነት ተደረገ

#FastMereja I የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ/ ፋውንዴሽን “በኢትዮጵያውያን የልብ ሐኪሞች – ለኢትዮጵያውያን ሕጻናት ልብ ጤና!!” በሚል መሪ ቃል በቅርቡ በአሜሪካን ሀገር ባሰባሰበው የገንዘብ ድጋፍ 170 የልብ ሕሙማን ሕፃናት ከሚያዝያ 12/2018 (April 20) ጀምሮ በ45 ቀናት ጊዜ ውስጥ ሕክምና ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት መጋቢት 20/2018 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል ፈጸመ። በስምምነቱ የተሳተፉት:-
1.የጤና ሚኒስቴር፣
2.የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣
3. የቅዱስ ጻውሎስ ሆስፒታል፣
4. የኢትዮጵያ ልብ ማኀበር፣
5.የኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ባለሙያዎች ማኀበር፣
6. የኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል፣
7.ጣዝማ ሜዲካል ኤንድ ሰርጂካል ስፔሻላይዝድ ሴንተር፣
8.ኤሊዘር የልብ ሕክምና፣ እንዲሁም የልብ ሐኪሞች ናቸው።

አቶ ብርሃን ተድላ የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ/ ፋውንዴሽን መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ እና የኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ባለቤት እንደተናገሩት ስምምነት ለፈፀሙ የጤና ተቋማት፣ ማኀበራትና ባለሙያዎች ያላቸውን አድናቆትና ክብር በመግለፅ ቀደም ሲል በኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ተጀምሮ የነበረው የልብ ሕሙማን ሕፃናትን የማከምና የመደገፍ ሥራ በኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንሰ ኤይድ በኩል ተደራሽነቱን ለማስፋትና በሕክምና ተቋማት ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ ስምምነት በመፈፀሙ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ስምምነቱ በሕክምና ወረፋ ረዥም ጊዜ ከማሳለፋቸው ጋር ተያይዞ ለሞት ጭምር የሚዳረጉ የልብ ሕሙማን ሕጻናትን ከመታደግ አንጻር የሚኖረው ትርጉም ላቅ ያለ መሆኑን እንዲሁም የኢትዮጵያ ጤና ተቋማትና ባለሙያዎች በትብብር እንዲህ አይነት ትልቅ ተልእኮ መወጣት እንደሚችሉ ምሳሌ የሆነ በመሆኑ ትብብሩን ልዩ እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል።

በስምምነቱ መሰረት በ45 ቀናት ጊዜ ውስጥ 170 ሕፃናት ሕክምናውን የሚያገኙ ሲሆን ፋውንዴሽኑ አስፈላጊውን ግብዐቶችና ወጪ በመሸፈን እንዲሁም የዚህን ተልእኮ በመምራትና በማስተባበር ሥራዎችን የሚያከናውን ሲሆን በመንግስትና የግል ሆስፒታሎቹ በኩል እንደአቅማቸው ያሏቸውን ባለሙያዎች በማስተባበር ሕክምናው በመስጠት፣ የታካሚዎች የቆይታ ጊዜ አስፈላጊውን እንክብካቤና ክትትል ያደርጋሉ።

ኸርት ቱ ኸርት በተጨማሪም ለዚሁ ሰብዓዊ ስራ ከጣልያን ሀገር የሚመጣው የሕክምና ቡድን የዚሁ ስራ አካል ሲሆን በቡድኑ ከሚታከሙ 50 ሕፃናት መካከል ግማሹ በፋውንዴሽኑ በኩል የሕክምና ግብዐት ወጪን ጨምሮ የቡድኑ የኢትዮጵያ የሆቴል ቆይታ ወጪ እንደሚሸፈን ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ዶ/ር አስቻለው ወርቁ በኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ የመሰረተው በጋራ የመሥራት ትብብር በአርአያነት የሚታይና ሚኒስቴሩም አቅም በፈቀደ ሁሉ የሚደግፈው መሆኑን በመጥቀስ አበረታተዋል።

ዶ/ር አስቻለው አያይዘውም ጤና ሚኒስቴር አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በስምምነቱ ላይ የተገኙ የረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸው የሆስፒታል ሥራ አስፈፃሚዎች፣ ዳይሬክተሮች እና የሕክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው የልብ ሕሙማን ሕጻናትን ለመታደግ በተፈጠረውና በጤና ዘርፍ በአርአያነት ጭምር ሊጠቀስ በሚችለው በዚህ ትብብር መደሰታቸውንና ለተፈጻሚነቱም የአቅማቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

አቶ ብርሃን ተድላ በመጨረሻም ለዚህ ታሪካዊ ትብብር ስኬት ከፍተኛ ድርሻ ላላቸው ሆስፒታሎች፣ የዘርፉ ማኀበራትና ባለሙያዎች ያላቸውን አድናቆትና ክብር በመግለፅ በኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ ቦርድ እና በታካሚ ሕጻናቱ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።





Leave a Comment