banner

አዲስ አበባ አህጉራዊ የሪል ስቴት ጉባኤና ኤክስፖን ልታስተናግድ ነው!

#FastMereja I የኢትዮጵያ የሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር “አዲስ አፍሪካ ሪል እስቴት ኤክስፖ 2026” የተሰኘውን የመጀመሪያውን አህጉራዊ የኤግዚቢሽን መድረክ በመጪው ሚያዚያ ወር በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ አስታወቀ።

ማህበሩ ከዶክሳ ኢቨንትስ ጋር በመተባበር ከሚያዚያ 15 እስከ 18 ቀን 2018 ዓ.ም በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሙዚየም ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚያካሂደው ይህ ታላቅ ኩነት፤ የኤክስፖውን ያህል ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን መርሀ-ግብሮችን የያዘ መሆኑንም ገልፀዋል።

በእለቱ ከሚከናወኑ መርሀ-ግብሮች የማህበሩ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ፣የአፍሪካ ሪል ስቴት ማህበር(AFRES) የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ጉባኤ እና አልሚዎች ያላቸዉን ያሏቸዉን ግብአቶች እና ፕሮጀክቶቿቸዉን ለህዝብ እና ለተሳታፊዎች የሚያሳዩባቸዉ መድረኮች መሆናቸዉ ተገልጿል።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አለማየሁ ከተማ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ሪል ስቴት ማህበር የአባላቱን መብት ከማስጠበቅ ባለፈ፣ ደንበኞች ጥራት ያለውና በውል በተገባው ጊዜ የሚረከቡትን ቤት እንዲያገኙ የሚያስችል የክትትልና የሙያ ስነ-ምግባር ደንብ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

በኤግዚቢሽኑ ላይ የሚሳተፉት የማህበሩ አባል የሆኑ ህጋዊና እውቅና ያላቸው አልሚዎች ብቻ በመሆናቸው፣ ቤት ፈላጊው ማህበረሰብ ካልተገባ እንግልት እንዲጠበቅ እንደሚያደርገው ተመልክቷል።

ይህ መድረክ በተለይ የማህበሩ አባላት የሆኑ አልሚዎች የተለያዩ የቤትና የህንፃ ፕሮጀክቶቻቸውን ይዘው የሚቀርቡበት በመሆኑ፣ ቤትና የንግድ ቦታ ፈለጊ ማህበረሰብ አማራጮችን በአንድ ቦታ እንዲያገኝ ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር ታውቋል።

ከሪል ስቴት አልሚዎች በተጨማሪ የፋይናንስ ተቋማት፣ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች እና ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት በዝግጅቱ ላይ የሚሳተፉ በመሆኑ ለዘርፉ እድገት ትልቅ አቅም ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነዉ የተገለፀዉ።

በኤክስፖው ላይ የሚሳተፉ የውጭ አገር እንግዶችና ባለሀብቶች አዲስ አበባ በቅርቡ ያስገነባቻቸውን አዳዲስ የቱሪስት መስህቦችና የኮሪደር ልማቶችን እንዲጎበኙ ፕሮግራም መያዙ ተያይዞ ተገልጿል።

ይህም አገሪቱ ከኮንፈረንስ ቱሪዝም የምታገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግና የአዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ዳግም ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

#ኹነት





Leave a Comment