banner

የኢትዮጵያ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ታሪክና የወደፊት አቅጣጫ የሚዳስሰው መጽሐፍ ተመረቀ!

#FastMereja I በኢትዮጵያ የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ገደማ የዘለቀ ልምድ ያካበቱት ዶ/ር አሸናፊ ፀጋዬ፣ የዘርፉን ታሪክና የወደፊት አቅጣጫ የሚተነትን” ሮድ ቱ ዲትሮይት” (The Road to Detroit)የተሰኘ አዲስ መጽሐፋቸውን በዛሬዉ እለት በሳፋየር አዲስ ሆቴል አስመረቁ፡፡

በሐራ ኢቨንትስ አስተባባሪነት በተዘጋጀው በዚህ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢነርጂ ዘርፍ ምሁራን፣ የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ይህ መጽሐፉ ደራሲው በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሳለፉትን የ48 ዓመታት ረጅም ጉዞ መነሻ በማድረግ፣ ዘርፉ ያለፈባቸውን ውጣ ውረዶችና ያስመዘገባቸውን ስኬቶች በዝርዝር የሚያሳይ ሲሆን በተለይም “ወደ ዲትሮይት የሚወስደው መንገድ” (The Road to Detroit) የሚለው ርዕስ፣ የዓለም አቀፉን አውቶሞቲቭ ማዕከል ዲትሮይትን ታሪክና ደራሲው ካሳለፉት ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ጋር በማስተሳሰር ነዉ ለንባብ የቀረበዉ።

መፅሀፉ 189 ገፆችን የያዘ ሲሆን ፅፎ ለማጠናቀቅ 9 ወራት እንደፈጀም በምረቃ ስነ-ስርአት ላይ ተገልጿል።

መጽሐፉ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ትኩረት እየተሰጣቸው ባሉት ነጥቦች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ዙሪያ ኢትዮጵያ ወደ አረንጓዴ ኢነርጂና የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች በምታደርገው ሽግግር ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ እድሎችና ተግዳሮቶችን እንደሚዳስስ ተገልጿል።

በምረቃው ወቅት ንግግር ያደረጉ የዘርፉ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፣ መጽሐፉ በተለይ ለትራንስፖርት ዘርፍ ተማሪዎች፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና በኢንዱስትሪው ውስጥ ለሚሰሩ መሐንዲሶች እንደ ዋቢ መጽሐፍ የሚያገለግል መሆኑን አንስተዋል።

ዶ/ር አሸናፊ ፀጋዬ በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለ48 ዓመታት በተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉ ሲሆን፣ በተለይም በዘርፉ በነበራቸው ዓለም አቀፍ ግንኙነትና የምክር አገልግሎት ይታወቃሉ፡፡





Leave a Comment