banner

የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የምስራቅ ኢትዮጵያን የቱሪስት መስህቦች ጎበኙ

​#FastMereja I በ”ቅን ልቦች” የበጎ አድራጎት ድርጅት የተዘጋጀውና በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ያሳተፈው «የሰላም ቱሪዝም ለሀገር ግንባታ» የጉብኝት መርሃ ግብር በድሬዳዋ፣ በማያ ከተማና በሐረሪ ክልል በድምቀት ተካሂዷል። ይህ ጉብኝት የሀገሪቱን የቱሪዝም ሀብቶች በማስተዋወቅና ሰላምን በመገንባት ረገድ ያለውን ፋይዳ ለማጎልበት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

​በጉዞው መጀመሪያ የቡድኑ አባላት በድሬዳዋ ከተማ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል። በንግድና በኢንዱስትሪ የምትታወቀው ድሬዳዋ፣ በዘመናዊ የከተማ ውበትና ለመንገደኞች ምቹ በሆኑ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ተገቢውን የቱሪስት መዳረሻነት እየተቀዳጀች መሆኑን ታዝበዋል። ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ በቆይታቸው የከተማዋን የቀድሞ ለውጥና የአሁኑን ገጽታ በማነጻጸር የተሰሩ ስራዎች ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዕድገት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

​የጉዞው ቀጣይ መዳረሻ የነበረችው የማያ ከተማ ሲሆን፣ በዚያም በአንድ ወቅት ደርቆ የነበረውና በአሁኑ ወቅት በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ጥበቃ ዳግም ህይወት የዘራው የሐረማያ ሐይቅ ተጎብኝቷል። የሐይቁ መመለስ ለአካባቢው ስነ-ምህዳርና ለቱሪስት መስህብነት ያለውን ሚና የተረዱት ተሳታፊዎቹ፣ የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ ለሀገር ግንባታ ያለውን ፋይዳ አጽንኦት ሰጥተውበታል። ይህ የሐይቁ መመለስ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ የፈጠረው ተስፋና ደስታም የጉብኝቱ ልዩ ትኩረት ነበር።

​በሐረሪ ክልል በተደረገው ጉብኝት ደግሞ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦድሪ በድሪ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፣ ተፅኖ ፈጣሪዎቹ በዩኔስኮ የተመዘገበውን ታሪካዊ የጀጎል ግንብን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ወቅት የሐረር የቆየ የመቻቻልና የፍቅር እሴት ለሰላም ቱሪዝም ግንባታ እንደ ምሳሌ የሚጠቀስ መሆኑ ተመላክቷል። ክልሉ ያለውን ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በስፋት ማስተዋወቅ እንደሚገባም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

​«የሰላም ቱሪዝም ለሀገር ግንባታ» የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ በዋናነት ቱሪዝምን እንደ አንድ የዲፕሎማሲና የሰላም ግንባታ መሳሪያ መጠቀም ላይ ያተኩራል። ሰዎች ከተለያዩ አካባቢዎች በመነሳት የሌላውን ባህል፣ ታሪክና እሴት ሲጎበኙ በመካከላቸው ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ጥላቻንና ጥርጣሬን ያስወግዳሉ። ይህም በተራው ለሀገራዊ አንድነትና ለጋራ ግንባታ መሰረት የሚጥል ሲሆን፣ ቱሪዝም በኢኮኖሚ ከሚያስገኘው ገቢ ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ያለውን ከፍተኛ ሚና ያመላክታል። ተጽዕኖ ፈጣሪዎቹም ይህንኑ እውነት በማህበራዊ ገጾቻቸው በማጋራት የሀገርን ገጽታ የመገንባት ሃላፊነት እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

📷 Visit Oromia





Leave a Comment