#FastMereja I በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ላሃ ከተማ ነዋሪ በሆነችው ነፍሰ ጡር እናት ዘሃራ ይማም ላይ የተፈጸመውን ዘግናኝ ግድያ ተከትሎ የአካባቢው የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት እና የላሃ ኑር መስጂድ ድርጊቱን በጽኑ የሚያወግዝ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።
የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ የተፈጸመው ይህ ግድያ፣ ማህበረሰቡን ለከፍተኛ ድንጋጤና ሀዘን ዳርጓል። ጉዳዩን አስመልክቶ የወጣው መግለጫ ድርጊቱን “አረመኔያዊና የሰው ልጅ የሞራል ውድቀት ማሳያ” ሲል የገለጸው ሲሆን፣ ወንጀሉ ከየትኛውም እምነትና ባህል ጋር እንደማይገናኝ አጽንኦት ሰጥቷል።
የመሎ ኮዛ ወረዳ እስልምና ጉዳይ እና የላሃ ኑር መስጂድ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ መንግስትና የፍትህ አካላት ወንጀለኛውን በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲያቀርቡና ከድርጊቱ ክብደት አንጻር የሚመጥን ከፍተኛ የህግ ቅጣት እንዲሰጡት ጠይቀዋል። “ጭካኔ ሃይማኖት የለውም” ያለው መግለጫው፣ አንዲትን ንጹህ ነፍስ መግደል መላውን የሰው ልጅ እንደመግደል የሚቆጠር መሆኑን በመጥቀስ፣ ማህበረሰቡ መሰል ጥቃቶችን በማጋለጥ ረገድ በአንድነት እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል።
ተጎጂዋ ዘሃራ ይማም በሁኔታው ህይወቷን ማጣቷ የተረጋገጠ ሲሆን፣ የፍትህ አካላት በጉዳዩ ላይ የጀመሩትን ምርመራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የአካባቢው ነዋሪዎች እየወተወቱ ይገኛሉ።
ድርጊቱ መጋቢት 28/2018 ዓ/ም ከምሽቱ 1:00 አከባቢ ታማሚ ልጇን አቅፋ፣ የ6 ወር እርጉዝ ሆና ሀገር ሰላም ነው ብላ ቁጭ ያለችውን ዘሀራን፣ የልጆቹን እናት፣ የትዳር አጋሯን እንደ በግ አስተኝቶ በቢላ ህይወቷ እንዲያልፍ በማድረጉ ቁጣን ቀስቅሷል።
