banner

ቬሮኒካ አዳነ ስለ ቴዲ አፍሮ ይህን ብላለች

#FastMereja I ታዋቂዋ ድምፃዊት ቬሮኒካ አዳነ፣ የኪነ-ጥበብ ንጉሥ በሚል የምትጠራው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) አዲስ አልበሙን ለረጅም ጊዜ የዘገየበትን ምክንያትና የግል ማንነቱን የሚገልጽ ምስክርነት ሰጠች። ቴዲ አፍሮ ሌሎች ድምፃውያን ስራቸውን ሲያወጡ የገበያ መደራረብ እንዳይፈጠርና የእነሱ ስራ እንዳይጎዳ በማሰብ የራሱን አልበም ወደ ኋላ ሲያቆይ እንደነበር ገልፃለች።

ድምፃዊት ቬሮኒካ አዳነ በማህበራዊ ገጿ ባሰፈረችው መረጃ፣ ቴዲ አፍሮን “በእውቀት፣ ዝናን በመቆጣጠር፣ ለሕዝብ በመቆም እና ታሪክን በማወቅ” ወደር የማይገኝለት ስትል ገልጻዋለች። ድምፃዊቷ ካሰፈረቻቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል፣ የቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም ዝግጅት ከሁለት ዓመት በፊት ተጠናቆ ሊወጣ ይችል እንደነበር ጠቁማለች። ይሁን እንጂ በተከታታይ ሌሎች ወጣትና አንጋፋ ድምፃውያን አልበሞቻቸውን ሲያወጡ፣ “እነሱ ላይ ደርቤ ስራቸው እንዳይበላሽ” በሚል ቅንነትና ሌሎችን የማክበር ስሜት ራሱን ወደ ኋላ ማድረጉን ገልጻለች።

በተጨማሪም ድምፃዊቷ ስለ ቴዲ አፍሮ መንፈሳዊ ጥንካሬ ስትመሰክር፣ ፈጣሪውን የሚያከብርና በጸሎት ቤት የሚተጋ ሰው መሆኑን ካሰፈረችው መረጃ ለመረዳት ተችሏል። “የጥበብ መከበር በተግባር ከለፉት ውስጥ አንደኛውና ዋናኛው ነው” ስትል የገለጸችው ቬሮኒካ፣ አሁን የሱ ሰዓት መሆኑንና መልካም ምኞቷን ገልጻለች።

Leave a Comment