#FastMereja I ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ሊሰጠው የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ በመንግስት ታገደ በሚል የሚናፈሰው መረጃ መሠረት የሌለው “የበሬ ወለደ” ፈጠራ መሆኑ ተገለጸ።
ባለፉት ቀናት በልዩ ልዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የድምፃዊ ቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም መግለጫ በመንግስት ጫና መታገዱን የሚገልጹ መረጃዎች በስፋት ሲሰራጩ ቆይተዋል። ሆኖም ጉዳዩን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፈዲላ ቢያ፣ መረጃው ከእውነት የራቀ መሆኑንና የታገደ መግለጫ አለመኖሩን አስታውቀዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከ50 በላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱባት ሀገር ሆና እያለች፣ የአንድ ዘፋኝ እንጉርጉሮ የሚታገድበት ምንም አይነት አግባብ የለም። “በሆነ መንገድ እገፋለሁ፣ እፈራለሁ፣ ተፅዕኖዬ ከባድ ነው የሚለውን ለራስ ከልክ በላይ ግምት በመስጠት ለማሳመን የሚደረግ ፈጠራ ደስ አይልም” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ትችት ሰንዝረዋል።
መንግስት በአሁኑ ወቅት ትኩረቱን ሀገርን ከድህነት በማላቀቅ፣ አሰባሳቢ ትርክቶችን በመፍጠር እና ኢትዮጵያን በሚገባት ልክ በመገንባት ላይ ማድረጉን የገለጹት ፈዲላ ቢያ፣ “መግለጫ አገደ” የሚለው ወሬ የብልፅግና መንግስት ስም የሚነሳበት አጀንዳ አለመሆኑን ገልጿል።
