banner

የቴዲ አፍሮ እና የሰዋሰው ውል መቋረጥ።

#FastMereja I በድምጻዊ ቴዲ አፍሮ እና በሰዋሰው መልቲሚዲያ መካከል የነበረው የአልበም ስርጭት ውል በስምምነት መቋረጡን ሰዋሰው ይፋ አደረገ። ለውሉ መፍረስ ዋነኛው ምክንያት የ”ኢትዮሪካ” አልበም የሙዚቃ ይዘት ሳይሆን፣ የጥሪ ድምጽ (CRBT) አገልግሎትን በማን ይተዳደር በሚል በተፈጠረ የንግድ ስምምነት ልዩነት መሆኑ ታውቋል።

ባለፉት ቀናት በድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) እና በሰዋሰው መልቲሚዲያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በተመለከተ ሲሰራጩ የነበሩ መረጃዎችን ተከትሎ ተቋሙ ዝርዝር መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫውም የሁለቱ አካላት ግንኙነት በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁንና ድምጻዊው ለሰዋሰው መክፈል የሚገባውን የሦስት ዓመት ከስምንት ወር ክፍያ ከወለድ ጋር መመለሱ ተረጋግጧል።

እንደ ሰዋሰው መግለጫ ከሆነ፣ ለውሉ መቋረጥ መነሻ የሆኑት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦

• የCRBT ውዝግብ፦ በውሉ መሠረት የጥሪ ድምፅ (CRBT) የመጠቀም መብት የሰዋሰው ቢሆንም፣ ድምጻዊው በዚህ ነጥብ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ በመጠየቁ የሃሳብ ልዩነት ተፈጥሯል።

• ያልተሳኩ አማራጮች፦ ሰዋሰው ድምጻዊው ተጨማሪ ክፍያ ተከፍሎት የቀድሞ ስራዎቹ ጭምር በመተግበሪያው ላይ እንዲጫኑ አማራጭ ቢያቀርብም ቴዲ አፍሮ አልተቀበለውም። በምላሹም ቴዲ አፍሮ “ከፊል አልበሙ በራሴ የዩቲዩብ ቻናል፣ ቀሪው በሰዋሰው ይለቀቅ” የሚል ሃሳብ ቢያቀርብም ሰዋሰው ሳይስማማ ቀርቷል።

• የይዘት ጉዳይ፦ “በአልበሙ ውስጥ ሰዋሰው የማይፈልጋቸው የሙዚቃ ስራዎች አሉ” በሚል የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን ተቋሙ ገልጾ፣ እስካሁን የአልበሙን ስራዎች እንዳልሰማቸው አረጋግጧል።

በመጨረሻም ሁለቱ አካላት በሰላምና በመከባበር መለያየታቸውንና ሰዋሰው ለድምጻዊው “ኢትዮሪካ” አልበም መልካም እድል መመኘቱን አስታውቋል።


Leave a Comment