#Fastmereja: በኢትዮጵያ የኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር (ASD) ያለባቸውን ሕፃናትና ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ ”ሳይንስን ለለውጥ” በሚል መሪ ቃል፤ ‘ሆፕ ፎር ስፔሻል ኢጁኬሽን” በማስረጃ ላይ የተደገፈ አሰራር (Evidence-Based Practice) ላይ ትኩረት ያደረገ ልዩ የስልጠና ፕሮግራም አጠናቆ 13 ባለሙያዎችን በዛሬዉ እለት አስመርቆ የሰርተፍኬት መርሀ-ግብር አከናዉኗል።
ስልጠናዉን በመዉሰድ ሰርተፍኬት የተሰጣቸዉ ባለሙያዎች በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ እና ወቅታዊ የሆኑ የድጋፍ መስጫ ዘዴዎችን እንዲቀስሙ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
በቤስት ዌስተርን ፕላስ ፐርል አዲስ ሆቴል በተካሄደው በዚህ የምረቃ እንዲሁም የሰርተፍኬት ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፤ ስልጠናው በተለይ የኦቲዝም ተማሪዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማርና ተጨባጭ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ክህሎቶች ላይ ትኩረት ማድረጉም ተገልጿል።
ለሁለተኛ ዙር በተሰጠው በዚህ ስልጠና 13 ባለሙያዎች የንድፈ-ሀሳብ ትምህርትን ከተግባራዊ ልምምድ ጋር አስተሳስረው በመውሰድ የምስክር ወረቀታቸውን መቀበላቸዉ ነዉ የተገለፀዉ።
የሆፕ ፎር ስፔሻል ኢዱኬሽን መስራች ወ/ሮ አይዳ አማረ በወቅቱ እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ ጥራት ያለው የልዩ ፍላጎት ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ የሰለጠነ የሰው ኃይል ወሳኝ ሚና አለው ሲሉ ተናግረዋል።
ወ/ሮ አይዳ አማረ አክለዉም “ይህ ፕሮግራም ተመራቂዎች በየተሰማሩበት የትምህርትና የሕክምና ተቋማት ውስጥ በማስረጃ ላይ የተደገፈ አሰራርን እንዲተገብሩና ለውጥ እንዲያመጡ ትልቅ በር ይከፍታል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከምረቃ መርሐ-ግብሩ በተጨማሪ በዕለቱ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲህ ያሉ ሙያዊ ስልጠናዎች በስፋት ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ማህበረሰቡ ስለ ኦቲዝም ያለው ግንዛቤ እንዲያድግና ለልዩ ፍላጎት ትምህርት የሚሰጠው ትኩረት እንዲጨምርም ጥሪ ቀርቧል።
ይህ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት በሀገሪቱ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ዘርፍ ውስጥ ያለውን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍና ለኦቲዝም ተገቢውን ትኩረት ለመስጠት ለሚደረገው ጉዞ እንደ አንድ ትልቅ እርምጃ ተወስዷል።




