#FastMereja I በአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች እየታየ ያለው ከፍተኛ የልማት ድጋፍ፣ ተነሳሽነት እና የሀገርን ገጽታ የመገንባት ስራ እጅግ አስደናቂና ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ ይህንን የገለጹት የወጣቶች ወቅታዊ ተሳትፎን እና በሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው። አስተዳደራቸው ለኢትዮጵያ ብልጽግና በትጋት እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች፣ ወጣቱ የዚህ ስራ ፍሬ ተቋዳሽ እና የሀገሪቱን ብልጽግና የሚያጣጥም ቀዳሚ ኃይል መሆኑን አስገንዝበዋል። በአሁኑ ወቅት ሀገራቸውን የሚወዱ እና ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ የሚተጉ ወጣቶችን መመልከት፣ ለከተማው አስተዳደርም ቢሆን በበለጠ ትጋት ለመስራት ትልቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥርለት በምሳሌነት አንስተዋል።
ከንቲባዋ ወጣቶች እያከናወኑት ላለው ተግባር በማሳያነት የጠቀሱት፣ ሰሞኑን እንደ አዶናይ ብርሃነ ያሉ ወጣቶች የዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ የመጋበዝ አዝማሚያን ነው። እነዚህ ወጣቶች እንደ ታዋቂው የአጫጭር ማህበራዊ ሚዲያ ዜና አቅራቢ ዲላን ፔጅ (Dylan Page) ያሉ ግለሰቦችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት የሀገሪቱን በጎ ገፅታ ለመገንባት እያከናወኑት ያለው ተግባር የሚበረታታ እና “ይበል” የሚያሰኝ መሆኑን በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል። በመሆኑም መላው ማህበረሰብ ለእነዚህ ወጣቶች “በርቱ!” በማለት ድጋፍ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።




