#FastMereja | የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ በሰው ሕይወት ማጥፋት ወንጀል ተከሰው ሲጠየቁ የቆዩት አቶ ጸጋዬ ታደሰ ላይ የሞት ቅጣት ውሳኔ አሳለፈ።
የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት፣ ለዛሬ ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም ቀጠሮ ይዞ የነበረውን የምርመራና የውሳኔ ሂደት በማጠናቀቅ ተከሳሹን በሞት እንዲቀጡ ወስኗል።
ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል ለግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም የነበረውን የቅጣት ውሳኔ ለመስማት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ በወቅቱ የቀረቡ የቅጣት ማቅለያ እና ማክበጃ ነጥቦችን ለመመርመር ለዛሬ ቀጠሮ አስተላልፎ ነበር።
በዛሬው የችሎት ውሎ፤ ተከሳሹ ካቀረቧቸው የቅጣት ማቅለያዎች መካከል ሁለቱን ፍርድ ቤቱ ተቀብሏል።በተመሳሳይ፣ አቃቤ ህግ ካቀረባቸው ልዩ የቅጣት ማክበጃዎች መካከል ሁለቱን ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ ተመልክቷል። ፍርድ ቤቱ የቀረቡትን የቅጣት ማቅለያና ማክበጃ ነጥቦች በአንክሮ በመገምገም፣ በሂደቱ የነበረውን የሞት ቅጣት መነሻ ውሳኔ በማጽናት የመጨረሻ ብይን ሰጥቷል።
የዲላ ማረሚያ ተቋም የተላለፈውን የሞት ቅጣት ውሳኔ ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ማስተላለፉን የጌዴኦ ዞን ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት መረጃ ያመለክታል።
