#FastMereja I ቻናል 1 ቴሌቪዥን ባስተላለፈው መዝናኛ ፕሮግራም ሳቢያ ህዝብን ይቅርታ ጠየቀ።
ቻናል 1 ቴሌቪዥን እሁድ ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም “እሁድን አንድ ላይ” በተሰኘው መዝናኛ ፕሮግራሙ ውስጥ፣ “ተረኛው ሐኪም” በሚል ንዑስ ክፍል “የመራቢያ አካላትን ማስዋብ ተጀመረ” በሚል ርዕስ ያሰራጨው ይዘት ከህግ እና ከህብረተሰቡ እሴት ጋር የሚቃረን መሆኑን በማመን ይፋዊ የይቅርታ መግለጫ አውጥቷል።
ጣቢያው ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የቀረበው ይዘት በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጾች ከተደነገጉት ግዴታዎች፣ በተለይም “ጨዋ የቋንቋ አጠቃቀም”፣ “የአካለ መጠን ያልደረሱ ህጻናትን ደህንነት መጠበቅ” እንዲሁም “የማህበረሰቡን ሞራልና ባህላዊ እሴቶች ማክበር” ከሚሉት መርሆዎች ጋር በእጅጉ የተጋጨ መሆኑን አምኗል።
የቻናል 1 ቴሌቪዥን አመራሮች፣ ፕሮግራሙ ህጻናት በሚመለከቱበት ሰዓት ያለ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መቅረቡ እና የርዕሰ ጉዳዩን ይዘት ከማህበረሰባችን ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሳይመዘን መሰራጨቱ የሙያ ስነምግባር ጥሰት እንደሆነ በመግለጽ፣ ይህንን ስህተት በመፈጸማቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ማዘን ገልጸዋል።
ጣቢያው ለወደፊቱ በህግና በስነምግባር መመሪያዎች መሰረት አገልግሎት ለመስጠት ቃል በመግባት፣ በፕሮግራሙ ሳቢያ ቅር ለተሰኙ አድማጭ ተመልካቾቹ በሙሉ ይቅርታ ጠይቋል።
