banner

ቅን ልቦች 33 አርአያዎችን በ15 ሚሊዮን ብር የወርቅ ሜዳሊያ ሊሸልም ነው!

#Fastmereja:-የቅን ልቦች የበጎ አድራጎት ድርጅት በማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች አወንታዊ እና ገንቢ ተጽዕኖ ላሳደሩ 33 አካላት እና አርአያ ዜጎች የሚሰጥ፣ በድምሩ የ15 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የወርቅ ሜዳሊያ እና ልዩ የዕውቅና ሽልማት ዝግጅት በዛሬዉ እለት በተሰጠ መግለጫ ይፋ አድርጓል።

ድርጅቱ ላለፉት ስድስት ዓመታት የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮችን ለሀገር፣ ለሰላም እና ለሀገራዊ እሴቶች ግንባታ ላዋሉ አካላት ዕውቅና ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣ የዘንድሮው መርሃ ግብር የየወሩ አሸናፊዎችን በአንድ ላይ የሚያወዳድር «የአሸናፊዎች አሸናፊ» መድረክ መሆኑ ተገልጿል። ውድድሩ በሁለት ዋና ዋና ዘርፎች የተከፈለ ነው፡፡

የመጀመሪያው ዘርፍ በቲክቶክ፣ ፌስቡክ፣ ዩቲዩብ እና ቴሌግራም አወንታዊ ሚና ለተጫወቱ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የተዘጋጀ ሲሆን፣ ለዚሁ ዘርፍ በድምሩ 180 ግራም ንጹህ ወርቅ ተመድቧል። በዚህም ለ1ኛ ደረጃ 50 ግራም፣ ለ2ኛ ደረጃ 30 ግራም፣ ለ3ኛ ደረጃ 20 ግራም ወርቅ የሚሸለም ሲሆን፣ ከ4ኛ እስከ 20ኛ ደረጃ ለሚያጠናቅቁ ተወዳዳሪዎች ልዩ የዕውቅና መርሃ ግብር ተዘጋጅቷል።

ሁለተኛው ዘርፍ «ሀገር ተስፋ የምታደርግባቸው አርአያ ዜጎች» በሚል የተሰየመ ሲሆን፣ በየመስኩ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ መምህራንን፣ ምሁራንን፣ ስራ ፈጣሪዎችን፣ የባህር እና የአየር ካፒቴኖችን፣ ዲዛይነሮችን እና የቱሪዝም ባለሙያዎችን ያካተተ ነው። ለዚህ ዘርፍ 100 ግራም ወርቅ የተመደበ ሲሆን፣ ለ1ኛ ደረጃ 50ግራም ፣ለ2ተኛ 30ግራም እንዲሁም ለ3ተኛ 20ግራም ወርቅ ይሸለማሉ።

ለዚሁ መርሃ ግብር የቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማት እና የዲጂታል ድምፅ መስጫ መተግበሪያ (Voting App) በማቅረብ ሳንቲፔ (SantiPay) እና ሰበዝ ቴክኖሎጂ (Sevez Technology) ከአዘጋጁ ጋር በጋራ እየሰሩ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የዓመቱን በጎ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመምረጥ ዜጎች nyekinlibochaward.org በኩል ድምጻቸውን መስጠት እንደሚችሉም ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም መርሃ ግብሩ ሀገርን በላቀ ጥበብ፣ እውቀት እና ጀግንነት ያገለገሉ ከ10 በላይ አንጋፋ የሀገር ባለውለታዎችን ልዩ የምስጋና እና የክብር ፕሮግራም አካቶ እንደሚያከናውን ከዝግጅቱ አስተባባሪዎች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Comment