#FastMereja I የካሜሩን የኢኮኖሚ ሚኒስትር አላሚን ኦስማን ሜይ የመነፅር መስረቅ ጥርጣሬ ጋር ተያይዞ ለኣምስት ቀናት ታስረው የቆዩ አራት የካሜሩን ጋዜጠኞች ያለ ምንም ክስ ከእስር መለቀቃቸውን ቢቢሲ እና የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በያውንዴ ከተማ በተካሄደ የመንግሥት ይፋዊ መርሃ ግብር ላይ ዘገባ በመስራት ላይ እያሉ ነበር።
እንደ ዘገባዎች ማብራሪያ፣ ሚኒስትሩ «ጠፋብኝ» ያሉት መነፅር በኋላ ላይ በራሳቸው የግል ተሽከርካሪ ውስጥ ተረስቶ ተገኝቷል። ቢሆንም ግን ጋዜጠኞቹ መነፅሩ ከተገኘ በኋላም ቢሆን ለተጨማሪ ቀናት በእስር ላይ እንዲቆዩ መደረጋቸው ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሯል።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች እና የካሜሩን የሙያ ማህበራት ድርጊቱን በፅኑ ኮንነዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች በተገኙበት መርሃ ግብር ላይ ጋዜጠኞቹ ብቻ ተለይተው መጠርጠራቸውንና ለእስር መዳረጋቸውን «የፕሬስ ነፃነት ላይ የተፈጸመ ጥቃት» ሲሉ የገለጹት ማህበራቱ፣ መንግሥት ይፋዊ ይቅርታ እንዲጠይቅ እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መብት እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።
ጋዜጠኞቹ መስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ከእስር ሲለቀቁ ምንም ዓይነት ይፋዊ ክስ እንዳልቀረበባቸው ታውቋል።
