banner

አርቲስት ኢቲቃ ተፈሪ በታሰሩት አቶ ታዬ ደንደአ ዙሪያ ያቀረበው ጥሪ ትኩረትን ሳበ

#FastMereja I ​ታዋቂው የአፋን ኦሮሞ ድምጻዊ አርቲስት ኢቲቃ ተፈሪ፣ በአሁኑ ወቅት በሕግ ጥላ ሥር በሚገኙት የቀድሞው የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ላይ የሚፈጸመው እስርና እንግልት እንዲቆም እና በነፃ እንዲለቀቁ በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ ጥሪ አቀረበ። አርቲስቱ በሰጠው አስተያየት፣ አቶ ታዬ ከልጅነታቸው ጀምሮ ስለ ህዝብ መብትና ጥቅም በጽናት ሲታገሉ የቆዩ፣ ከሙስና እንዲሁም ከማንኛውም የደምና የስርቆት ወንጀል ነፃ የሆኑ እውነተኛ የህዝብ ተቆርቋሪ ናቸው ብሏል።

​አርቲስት ኢቲቃ ተፈሪ አክሎ እንደገለጸው፣ አቶ ታዬ ደንደአ በጽኑ አቋማቸውና በግልጽ ተናጋሪነታቸው ሰዎችን ያስቀየሙበት አጋጣሚ ሊኖር ቢችልም፣ ከግል ጥቅማቸው ይልቅ የጋራንና የህዝብን ጥቅም ያስቀደሙ ሰው መሆናቸውን ገልጿል። “ከእሳቸው በላይ ለህዝብ መብት ከፊት ቀድሞ የቆመ አካል የለም” ያለው አርቲስቱ፣ አገሪቱ ውስጥ በርካታ ጥፋተኞች በነፃነት እየተዘዋወሩ ባሉበት ሁኔታ እንዲህ ያሉ ጠንካራና አቋመኛ ሰዎችን ማሰርና ማንግላታት ለችግሮች መፍትሔ እንደማይሆን አስገንዝቧል።

​በመጨረሻም አርቲስት ኢቲቃ ተፈሪ ለሚመለከታቸው የመንግሥትና የፍትሕ አካላት ጥሪ በማቅረብ፣ አቶ ታዬ ደንደአ ከእስር ተፈተው ወደ ህዝባቸው እንዲመለሱ እና አላስፈላጊ እንግልት እንዲቆም መጠየቁን በግል የማህበራዊ ሚዲያ ገጹ ባሰራጨው መልእክት መመልከት ተችሏል።





Leave a Comment