banner

ሐበሻ ቢራ ኢትዮጵያ ቡናን በ45 ሚሊዮን ብር ስፖንሰር አደረገ

​
#FastMereja I ​ሐበሻ ቢራ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩውን ከሚያከብረው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ጋር የነበረውን አጋርነት ማደሱን ይፋ አደረገ። የመጀመሪያ ምርቱን ለገበያ ከማውጣቱ ከአንድ ዓመት በፊት ከክለቡ ጋር አብሮ መስራት የጀመረው ሐበሻ ቢራ፤ አሁን ደግሞ ድጋፉን በማሳደግ ከእያንዳንዱ የቢራ ጠርሙስ ሽያጭ ድርሻ ማጋራት የሚያስችለውን አዲስ ስምምነት ተፈራርሟል። የስምምነት ፊርማው የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች በተገኙበት ተከናወኗል።

​በዚህ አዲስ ስምምነት መሠረት ሐበሻ ቢራ የዘንድሮውን ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ ያደገ ሲሆን፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእያንዳንዱ የሐበሻ ቢራ ሽያጭ ላይ ለክለቡ ተጨማሪ ገቢ ለማጋራት ወስኗል። ይህም የቢራ ፋብሪካው ባደገ ቁጥር ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የሚሰጠው ድጋፍ አብሮ የሚያድግበትን አሰራር የዘረጋ መሆኑ ተገልጿል።

ስምምነቱ ክለቡ አዳዲስ አመራሮችን ወደ ኃላፊነት እያመጣ ባለበት ወቅት የተደረገ ሲሆን፣ ሐበሻ ቢራም የዚህ አዲስ ምዕራፍ አካል ለመሆን ያለውን ጽኑ ፍላጎት አረጋግጧል።

​የሐበሻ ቢራ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደገለጹት፤ “12 ቁጥር ለባለ 12 ለባሾቹ የቡና ደጋፊዎች ለክለባቸው ያላቸው ፍቅር እና ድጋፍ በከፍታውም በዝቅታውም ጊዜ እንደማይቋረጥ ሁሉ፤ እኛም እንደዚሁ ነን” ብለዋል። አክለውም ድጋፋቸው ከክለቡ ጎን ለመቆም ባላቸው የማይናወጥ ጽኑ ቁርጠኝነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው፤ የክለቡ የተሳካ የ50 ዓመታት ጉዞ የሁሉም ባለድርሻ አካላት እና ደጋፊዎች የጋራ ጥረት ድምር ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና ሀበሻ ቢራ ስፖንሰርሺፕ ለመጪው 3 አመታት 45 ሚሊዮን ብር ተፈራርሟል። በተጨማሪም ከቢራ ሽያጭ ላይ የሚሰበሰበ ከ13 እስከ 15 ሚሊዮን ብር በአጠቃላይ ከ58 እስከ 60 ሚሊዮን ብር ይደርሳል። ክለቡ ዋንጫ ካነሳ ተጨማሪ 15 ሚሊዮን ብር ለመስጠት ቃል ገብቷል።

​በመጨረሻም ሐበሻ ቢራ ለክለቡ እና ታማኝ ለሆኑት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል። በተጨማሪም ባለፉት አምስት አሥርታት ክለቡን ከጀርባውም ከፊቱም ሲደግፉ ለቆዩ ወገኖች በሙሉ ምስጋናውን አቅርቧል።





Leave a Comment