banner

አዋሽ ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር አምስት አዳዲስ የክፍያ ካርዶችን ይፋ አደረገ

​
#FastMereja I ​አዋሽ ባንክ ከአለም አቀፉ የክፍያ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ማስተርካርድ ጋር በመተባበር፣ የደንበኞችን ፍላጎት ያማከሉ አምስት አዳዲስ እና ልዩ ጥቅም የሚያስገኙ የውጭ ምንዛሬ እንዲሁም የሀገር ውስጥ የክፍያ ካርዶችን ይፋ አደረገ። ባንኩ መስከረም 28 ቀን 2019 ዓ.ም. በኢሊሊ ሆቴል ባካሄደው ይፋዊ ስነ-ስርዓት፣ አዲሶቹን የካርድ ክፍያ አማራጮች ለግል ተጠቃሚዎች እና ለድርጅት ደንበኞች አስተዋውቋል። አዲሶቹ ካርዶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ገበያን ለማሻሻል ካወጣው መመሪያ ጋር ተጣጥመው የተዘጋጁ መሆናቸው ተገልጿል።

​በዚህም መሰረት ይፋ ከተደረጉት አምስት የካርድ አይነቶች መካከል ለአለም አቀፍ ግብይት የሚያገለግሉት፡- “አዋሽ ወርልድ ኤሊት ዴቢት” (Awash World Elite Debit)፣ “አዋሽ ፕላቲነም የቅድመ ክፍያ” (Awash Platinum Prepaid)፣ “አዋሽ ጎልድ የቅድመ ክፍያ” (Awash Gold Prepaid) እና ለድርጅቶች የታለመው “አዋሽ ኮርፖሬት የቅድመ ክፍያ” (Awash Corporate Prepaid) ካርዶች ይገኙበታል። በተጨማሪም በሀገር ውስጥ በኤቲኤም (ATM) እና በPOS መሳርያዎች ላይ በንክኪ አልባ (Contactless) ቴክኖሎጂ የሚሰራው “አዋሽ ፕላስ” የዴቢት ካርድ ለተጠቃሚዎች ቀርቧል።
እነዚህ ካርዶች የውጭ ምንዛሬ ሂሳብ ላላቸውም ሆነ ለሌላቸው ዜጎች፣ ለኦንላይን (E-Commerce) ግብይት፣ ለጉዞ እና ለተለያዩ የድርጅት ወጪዎች አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው።

​በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአዋሽ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፀሐይ ሺፈራው እንደገለጹት፤ አዲሶቹ የካርድ ምርቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወሰደው የፋይናንስ ሪፎርም መሰረት የተዘጋጁ እና የደንበኞችን የዲጂታል ክፍያ ፍላጎት ዘመናዊ በሆነ መንገድ የሚያሟሉ ናቸው። የማስተርካርድ ምስራቅ አፍሪካ እና ህንድ ውቅያኖስ ደሴቶች ሲኒየር ምክትል ፕሬዚዳንት እና ካንትሪ ማኔጀር ሸህሪያር አሊ በበኩላቸው፣ ከአዋሽ ባንክ ጋር የተደረገው ይህ አጋርነት በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ስነ-ምህዳርን ለማጠናከር እና አካታች የፋይናንስ አገልግሎትን ለማስፋፋት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

​አዲሶቹ የካርድ ምርቶች ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ለአጠቃቀም ቀላል እና ደንበኞች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያሉ የዲጂታል ክፍያዎችን በቅልጥፍና እንዲፈጽሙ የሚያስችሉ መሆናቸው ተመላክቷል።





Leave a Comment