#Fastmereja:-ትክክለኛና በቂ እረፍት ለሰው ልጅ አካላዊና አእምሮአዊ ጤና፣ ለትምህርት አፈጻጸም እንዲሁም ለሥራ ምርታማነት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ያለመ “REST FOR WHAT MATTERS – እረፍት እንዲሳካ” የተሰኘ ሀገር አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ ይፋ ተደረገ።
በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደ የይፋ ማድረጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፤ ዘመቻው በማለዳ ፎም አዘጋጅነት የቀረበ ድርጅታዊ ማኅበራዊ ኃላፊነት ላይ ያተኮረ ንቅናቄ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም ማህበረሰቡ ለዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው፣ ለቤተሰብ ደህንነቱና ለሙያዊ ስኬቱ በቂ እረፍት መስጠት ያለውን አስፈለጊነት እንዲገነዘብ ማድረግ መሆኑ ተገልጿል።
በዝግጅቱ ላይ እንደተብራራው፣ ብዙ ጊዜ እረፍት ከምርታማነትና ከዕድገት ጋር እንደሚጋጭ ተደርጎ የሚወሰድበትን የተሳሳተ አመለካከት በመቀየር፣ እረፍትን ለሰው ልጅ አጠቃላይ ስኬትና ለሀገር ልማት መሠረት እንደሆነ የሚያሳይ አኗኗርን ማጎልበት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተገልጿል።
ዘመቻውን በፈጠራዊ መንገድ ተደራሽ ለማድረግም ማለዳ ፎም ከሰው መሆን ፊልምስ ጋር የአጋርነት ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን በዚህም መሠረት የዘመቻው መልዕክት በፈጠራዊ ታሪክ አቀራረብ፣ በድምፅና ምስል ይዘቶች እንዲሁም በሰፊው ሕዝብ ተሳትፎ ለህብረተሰቡ እንደሚደርስ ተመልክቷል።
በንቅናቄው ሥር የባለሙያዎች ውይይት፣ የእረፍት ፌስቲቫሎች፣ ኤግዚቢሽኖች እና የጎዳና ላይ ትዕይንቶች፣ የእረፍትና የስኬትን ግንኙነት የሚያሳዩ የአጭር ፊልም ፌስቲቫሎችን እንዲሁም ሌሎች ትዕይንቶች እንደሚደረጉ ተገልጿል።
ይህ ዘመቻ በጊዜ ሂደት እየተስፋፋ የሚሄድና ማህበረሰቡ ለበቂ እረፍትና ደህንነቱ ቅድሚያ የሚሰጥበትን አኗኗርየሚያጎለብት ቀጣይነት ያለው የማህበራዊ ኃላፊነት መድረክ እንደሚሆን ተመልክቷል።




