banner

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የዳንስና ውዝዋዜ አዋርድ ሊካሄድ ነዉ!

#Fastmereja:-በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዳንስና ውዝዋዜ ሙያ ላይ ብቻ ያተኮረው “ዳንኪራ የዳንስ/ውዝዋዜ አዋርድ” የዝግጅት ምዕራፉን አጠናቆ በይፋ መጀመሩ ተበሰረ።

ራስ አፍሮ ኪን ፕሮሞሽን በአዲስ አበባ የህፃናትና ወጣቶች ቲያትር አዳራሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ሽልማቱ በዘርፉ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ክብርና ዋጋ ከፍ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅና ባለቤት፣ በኢትዮጵያ አይዶል የመጀመሪያው የግል ዳንስ አሸናፊና በሀገር ፍቅር ቲያትርቤት በኮሪዮግራፈርነት ያገለገለው ወጣት አስጨናቂ በቀለ (ራስአፍሮ) እንደገለጸው፣ አዋርዱ “የኢትዮጵያ የዳንስ ከፍታ ራስን ከማክበር ይጀምራል” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን፤ በፊልምና በሙዚቃ ቪዲዮዎች ውስጥ ተገቢው እውቅና ሳይሰጠው የቆየውን የኮሪዮግራፈሮችና የዳንሰኞች ክፍተት መሙላት፣ አዳዲስ ወጣቶችን ማፍራትና የዘርፉን ተቀባይነት ማሳደግ ዋና ዓላማው ያደረገ ስለመሆኑም ነዉ የገለፀዉ።

ይህ አዋርድ በሴትና በወንድ በድምሩ 19 የሽልማት ዘርፎች የተዘጋጁ ሲሆን፤ ዘመናዊና ባህላዊ ዳንሰኞች፣ ኮሪዮግራፈሮች፣ በቲያትር፣ በፊልም፣ በሙዚቃ ቪዲዮዎች እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ (ቲክቶክን ጨምሮ) የሚሳተፉ የውዝዋዜ ባለሙያዎች ይሸለሙበታል።

የአሸናፊዎች አወሳሰን ሥርዓት 35% በዳኞች፣ 35% በእጩዎቹ እርስ በርስ ምርጫ እንዲሁም 30% በሕዝብ ድምፅ የሚወሰን መሆኑ ነዉ የተገለፀዉ።

እንዲሁም በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ውዝዋዜ ያስጠራውና በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የአንጋፋው አርቲስት ታደሰ ወርቁ ባልቻ ስም ለዘላቂው የአዋርዱ “የሕይወት ዘመን ተሸላሚ” መታሰቢያ ተደርጎ ተሰይሟል።

በዝግጅቱ ላይ ለዳንስ ጥበብ እድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱና በቅርቡ በሕይወት የተለዩት ፍሬሕይወት ባሕሩ፣ ኪዳኔ ምስጋናው፣ ወጣት ጳውሎስና ወጣት ዮናስ በአንድ ደቂቃ የዝምታ ጊዜ እንዲታሰቡ ተደርጓል።

ለ40 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር በዳንስ፣ በትወና፣ በድምፃዊነትና በዜማ ደራሲነት ያገለገሉት አንጋፋው አርቲስት ሰለሞን ተካ፣ የዳንኪራ ዳንስ አዋርድ የክብር አምባሳደር ሆነው ተመርጠዋል። የክብር ካባና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።

ሙሉ በሙሉ በዳንሰኞች አዘጋጅነትና መሪነት የሚካሄደው ይህ አዋርድ የዳንስና ውዝዋዜ ሙያን እንደ አንድ የጥበብ ዘርፍ ለማጠናከር፣ የሥራ ዕድሎችን ለማስፋትና የኢትዮጵያን ባህላዊና ዘመናዊ የዳንስ ቅርሶች ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ መሆኑ በመግለጫዉ ተብራርቷል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የጥበብ ባለውለታዎች፣ የዳንስና ውዝዋዜ ባለሙያዎች፣ የሙዚቃ ዘርፍ ተዋናዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኘ ሲሆን፣ አዋርዱ የዳንስ ሙያ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝና ወጣት ተሰጥኦዎች በተስፋ እንዲቀጥሉ የሚያስችል አዲስ የጥበብ መድረክ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።





Leave a Comment