#FastMereja I ተገኝ መውደድ የተባለ ተጠርጣሪ ወንጀሉን የፈፀመው ጥቅምት 17 ቀን 2019 ዓ.ም በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው አንፎ ኬላ አካባቢ በግምት ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ገደማ ነው።
የግል ተበዳይ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ3-07482 ሱ/ማ የሆነ መኪና እያሽከረከሩ በነበረበት ወቅት ግለሰቡ አንፀባራቂ ልብስ ለብሶ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪ ነኝ በማለት የግል ተበዳይን አስቁሞ የትራፊክ ደንብ ጥሰሻል በሚል የመንጃ ፍቃዳቸውን ከተቀበለ በኃላ ወደ ቢሮ ትሄጃለሽ በማለት መኪናው ውስጥ ገብቶ እንቅስቃሴ ይጀምራሉ።
የተወሰነ መንገድ እንደተጓዙም ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ታግተሻል እኔ ወደ ምልሽ ቦታ መኪናውን አሽከርካሪ በማለት ሽጉጥ አውጥቶ ያስፈራራቸዋል።
የግል ተበዳይ ለጊዜው ሽጉጡን ሲያዩ ቢደናገጡም መኪናውን እያሽከረክሩ የፖሊስ አባላትን ሲመለከቱ ባሰሙት የድረሱልኝ ጥሪ ግለሰቡ ወደ ሰማይ አንድ ጥይት ተኩሶ ለማምለጥ ቢሞክርም በቁጥጥር ስር መዋሉን የክፍለ ከተማው ፖሊስ ዋና መምሪያ አስታውቋል።
ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ የፍርድ ቤት መበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት የመኖሪያ ቤቱ ሲፈተሽ ለወንጀል መፈፀሚያ የሚጠቀምበት 1 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ከመሰል 14 ጥይት ጋር፣ አንፀባራቂ ልብስና 1 ሳንጃ እንዲሁም ብዛት ያላቸው የተሰረቁ የኤሌክትሪክ ገመዶች በተጨማሪ መገኘቱን ፖሊስ ገልጿል።
ፖሊስ እንዳለው አንፀባራቂ ልብስ በመልበስና ህጋዊ በመምሰል ወንጀል የሚፈፅሙ ግለሰቦችን ለመከላከል ህጋዊነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያና ባጅ እንዳላቸው ህብረተሰቡ ማረጋገጥ ይኖርበታል። ወንጀል ከተፈፀመም በአፋጣኝ ለፖሊስ ማሳወቅ እንደሚገባ መልዕክቱን አስተላልፏል።
Via Addis Ababa Police
