#FastMereja I የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥቅምት 20 ቀን 2019 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ፣ ቀደም ሲል በአጀንዳነት ሲመረመሩ የቆዩትን የጋምቤላ እና የቤንሻንጉል ጉምዝ አሶሳ ሀገረ ስብከቶች ጉዳይ መርምሮ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል (ረ/ፕ) ገለጹ። እንደ መምህር ዳንኤል መግለጫ፣ በአጣሪ ልዑካን የቀረቡ የሰነድ ማስረጃዎችን፣ የሂሳብና ንብረት ቁጥጥር ሪፖርቶችን መሠረት በማድረግ ውይይት ተደርጓል።
በወቅቱ የአህጉር ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ለተፈጠሩት ጥፋቶች በጉባኤው ፊት በአካል ቀርበው ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን፣ የይቅርታ ጥያቄያቸውን በጽሑፍም አቅርበዋል። ምልአተ ጉባኤው የብፁዕነታቸውን የይቅርታ ደብዳቤ በንባብ ከመረመረ በኋላ በተነሱት የቀኖና ጥሰቶች፣ የአስተዳደርና የአሠራር ክፍተቶች ዙሪያ በሰፊው በመወያየት የቀኖና እና አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን አሳልፏል። በዚህም መሠረት ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል እስከ ግንቦት 2019 ዓ.ም የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ድረስ በየትኛውም ሀገረ ስብከት ሳይመደቡ በደብረ ሊባኖስ ቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም በጸሎትና በሱባኤ እንዲቆዩ፣ ወደ ገዳም ከመሄዳቸው በፊት ለአህጉር ስብከት ማስረከብ የሚገባቸውን መኪኖች ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዲያስረክቡ፣ እንዲሁም ከሂሳብ ጋር የተያያዘው ጉዳይ እስከ ግንቦት ርክበ ካህናት እንዲጣራ ወስኗል።
በተጨማሪም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ክፍት በሆኑ አህጉር ስብከቶች ላይ ብፁዓን አባቶችን መድቧል። በዚህ መሠረት ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከትን ደርበው እንዲመሩ፣ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ (ዶ/ር) የጋምቤላ ሀገረ ስብከትን ደርበው እንዲመሩ፣ እና ብፁዕ አቡነ ሰላማ የሰቲት ሁመራና ወልቃይት ጠገዴ ሀገረ ስብከትን ደርበው እንዲመሩ ተወስኗል። ምልአተ ጉባኤው በእለቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን የተመለከተ የአጣሪዎች ሪፖርት በማዳመጥ እና የብፁዕ አቡነ ሕርያቆስንና የአስተዳደር ጉባኤ አባላትን ምላሽ በመመልከት ውይይቱን መቀጠሉን የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ዘገባ አመልክቷል።
