banner

ፖወር ጂም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን 30 የዘመናዊ የአካል ብቃት ባለ

ፖወር ጂም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን 30 የዘመናዊ የአካል ብቃት ባለሙያዎች በደማቅ ሁኔታ አስመረቀ

#FastMereja I የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከ«ፓወር ጂም» ጋር በመተባበር በከተማዋ የስፖርት ልማት ለማጠናከር፣ አትሌቶችን በአቅም ለመገንባት እና ለወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድል ፈጠራን ለመፍጠር ያለመውን የትብብር ስራ ውጤት አስመዝግቦ 30 የዘመናዊ የአካል ብቃት ባለሙያዎችን በይፋ አስመረቀ።

በፓወር ጂም እና በቢሮው መካከል የተደረገውን የመግባቢያ ሰነድና የትብብር ማዕቀፍ ተግባራዊ ለማድረግ የተከናወነው ይህ መርሃ ግብር፣ በከተማዋ የአካል ብቃት ዘርፍ የባለሙያ አቅምን ለማሳደግ ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑ ተገልጿል።

ለሦስት ወራት ያህል ሲሰጥ የቆየው እና በአጠቃላይ 63 ሰዓታት የፈጀው ጥልቅ ሥልጠና፤ የጽሁፍ እና የተግባር ክንውኖችን ያካተተ ነበር። የሥልጠናው ይዘት በዋናነት አናቶሚና ፊዚዮሎጂ፣ ፈርስት ኤይድ (የመጀመሪያ እርዳታ)፣ ኒውትሪሽን ሳይኮሎጂ እና ፊትነስ የመሳሰሉ ወሳኝ የሙያ ዘርፎችን የሸፈነ ሲሆን፣ ለአሰልጣኞች በዘርፉ ብቁና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እውቀቶችን እንዲጨብጡ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል። ሰልጣኞቹ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሳይንሳዊ ዕውቀት እንድጨብጡ ለማድረግም 5 የሜዲካል ዶክተሮች እና የፒኤችዲ (PhD) ባለቤቶች ሥልጠናውን በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

የፓወር ጂም አስተዳደር እንደገለጸው፣ ተቋሙ በዘርፉ የንግድ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ዘርፉን በብቁ ባለሙያዎች የማፍራት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየወጣ ይገኛል። ከከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር የተጀመረው ይህ አጋርነት የሙያ ዕውቀትን በስፋት ለማዳረስ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለገበያ ለማቅረብ የተወሰደ ወሳኝ ተግባራዊ እርምጃ መሆኑ ተነግሯል።

ለቀጣይ የስራ አፈፃፀምም ፖወር ጂምና የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የተፈራረሙትን የትብብር ማዕቀፍ በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል በመደበኛ የክትትልና የግምገማ ሥርዓት በቅርበት አብረው እንደሚሠሩ ተረጋግጧል። የዚህ የመጀመሪያ ዙር 30 ሰልጣኞች ማጠናቀቅ በከተማዋ የሚገኙ የስፖርት ስልጠና ማዕከላትን ለማዘመን እና ዘመናዊ የአካል ብቃት አሰራርን ለማስፋፋት ትልቅ መሰረት የሚጥል መሆኑ ተነግሯል።





Leave a Comment