banner

ዘጸአት ጉዞ እና ጉብኝት ይፋዊ የስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩን አካሄደ

​
#FastMereja I ዘጸአት ጉዞ እና ጉብኝት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዛሬ ጥቅምት 21 ቀን 2019 ዓ.ም ይፋዊ የስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩን በአዲስ አበባ በሚገኘው ክሪሰንት ኢንተርናሽናል ሆቴል በደማቅ ሁኔታ አካሂዷል። ድርጅቱ ዋነኛ ትኩረቱን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጉዞዎች ላይ በማድረግ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሀገር ዜጎች ታሪካዊና መንፈሳዊ መዳረሻዎችን በዕውቀት፣ በምክንያት እና ለበረከት እንዲጎበኙ ለማስቻል የተቋቋመ መሆኑ ተገልጿል። በተጨማሪም ከመላው ዓለም የሚመጡ የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት የሀገሪቱን ቅዱሳት መካናት፣ ገዳማት እና የቱሪዝም መዳረሻዎች የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ ተመላክቷል።

​ተጓዦች ወደተለያዩ መዳረሻዎች ለመጓዝ ፈልገው ሙሉ ክፍያ በአንድ ጊዜ ለመክፈል አቅም ለሚያንሳቸው ደንበኞች ታሳቢ ያደረገ የብድር የጉዞ አማራጭ ማዘጋጀቱ ተገልጿል። ይህም አሰራር ከፋይናንስ ተቋማትና ከባንኮች ጋር በተደረገ ስምምነት መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን መመሪያ ተከተሎ የሚፈጸም መሆኑ ተብራርቷል።

​ከተለያዩ የሙያ መስኮች በተወጣጡ ባለሙያዎች የተመሰረተው ዘጸአት ጉዞ እና ጉብኝት፤ ድርጅቱን ለቀጣይ አንድ ዓመት እንድታስተዋውቅ አርቲስት ቃልኪዳን አበራን ብራንድ አምባሳደር አድርጎ የሾመ ሲሆን፣ ዘፀአት ከኢምፓየር ቢዝነስ ግሩፕ እና ከጎዶልያስ ጋር አብሮ ለመስራት የጋራ ስምምነት ተፈራርሟል።

​በመጨረሻም በመርሃ ግብሩ ላይ በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ ላበረከቱት ላቅ ያለ አስተዋፅኦ ለሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የክብር ሽልማት የተበረከተ ሲሆን፤ ለጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፣ ለተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም እንዲሁም ለይዘት ፈጣሪው አቤል ብርሃኑ (የወይኗ ልጅ) የእውቅናና የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።





Leave a Comment