banner

“የህዝብ ድምፅ” ንግድ ሆነ

#FastMereja I በዓለም አቀፍ ደረጃ በውበት እና በኪነ-ጥበብ ውድድሮች ላይ እየታየ ያለው የህዝብ ድምፅን በገንዘብ የማስከፈል አሰራር፣ አሁን ላይ ወደ አገር ውስጥ የዕውቅና መድረኮች (አዋርዶች) በመዘዋወር ላይ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እየተዘጋጁ የሚገኙ የተለያዩ የሽልማት መርሃ-ግብሮች የህዝብ ድምፅን ከንግድ ጋር እያያዙት ይገኛሉ የሚለው ሀሳብ ከፍተኛ ትችት እያስነሳ ይገኛል።

እንደ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች፣ ለምሳሌ በቅርቡ በተካሄደው “ሚስ ወርልድ” (Miss World) ውድድር ላይ ተወዳዳሪዎች የመጀመሪያውን ድምፅ በነፃ መስጠት የሚችሉ ሲሆን፤ ተጨማሪ ድምፅ ለመስጠት ግን የውጭ ምንዛሬ (ዶላር) ክፍያ የሚጠይቅ አሰራር ተዘርግቶ ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን እና ናይጄሪያውያንን ጨምሮ በርካታ አህጉራዊ ተወዳዳሪዎች ደጋፊዎች ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው ድምፅ የሰጡ ቢሆንም፣ አሸናፊ መሆን ሳይችሉ ቀርተው የወጣው ገንዘብ ለአዘጋጆቹ ገቢ ሆኖ መቅረቱ ይታወሳል።

ይህ አሰራር አሁን ላይ ሀገር ውስጥም ሥር እየሰደደ መምጣቱ እየተነገረ ነው። በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ የሚዘጋጁ በርካታ የዕውቅና እና የሽልማት መድረኮች “የህዝብ ድምፅ” የሚል መጠሪያ እየተጠቀሙ ቢሆንም፣ በተጨባጭ ግን ድምፁ ከክፍያ ጋር የተያያዘ እና በገንዘብ አቅም የሚወሰን እየሆነ መምጣቱ ተገልጿል፡፡ ይህም ተወዳዳሪዎችን እውነተኛ ተወዳዳሪነት የሚፈትን እና ሂደቱን አድሎአዊ የሚያደርግ መሆኑ በባለሙያዎች ይነገራል።

“የህዝብ ድምፅ” የተሰኘው ሂደት ማንነቱ እስከተጠበቀ ድረስ ሙሉ በሙሉ እና ያለምንም የገንዘብ ክፍያ በነጻ መከናወን ይኖርበታል። የህዝብን ፍላጎት እና ምርጫ በገንዘብ መሸጥ ተገቢ ያልሆነ አሰራር መሆኑን በመገንዘብ፣ አዘጋጅ አካላት ይህንን አሰራር ሊያስተካክሉት እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎች አሳስበዋል።

Leave a Comment