banner

10 ሚሊዮን ብር የወጣበት የድምጻዊት ሄለን በርሄ “የበረታ” አዲስ የሙዚቃ አልበም

#FastMereja I “ታስፈልገኛለህ” እና “እስኪ ልየው” የተሰኙ ሁለት አልበሞችን ለአድማጮች ያደረሰችው ድምጻዊት ሄለን በርሄ፣ “የበረታ” የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ አልበሟ ተለቀቀ። ይህ የሙዚቃ አልበሟ የሚወጣው ሁለተኛ አልበሟ ከታተመ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ነው።

በሸራተን አዲስ ሆቴል ድምጻዊቷ እና በአልበሙ ላይ የተሳተፉ የሙዚቃ ባለሞያዎች በተገኙበት ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። በዚህም መግለጫ ላይ አልበሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ አምስት ዓመታት እና ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ እንደፈጀ ተገልጿል።

ቀደም ሲል ከወጡት፣ ሁለት የድምጻዊቷ አልበሞች ይህ አዲሱ አልበም ለየት የሚያደርገው ለሁሉም ዘፈኖች ደረጃውን የጠበቀ ቪዲዮ ክሊፕ መሰራቱ እንደሆነ ሲነገር፣ ይህም በብዙ ውጣ ውረድ ሊጠናቀቅ ስለመቻሉ ነው የተብራራው። ድምጻዊት ሄለን በርሄ ስትናገር፣ ከቤተሰብ እና ከምሽት ክበብ ስራ የተረፈ ጊዜዋን በዚህ አልበም ላይ ለማዋል ጥረት ማድረጓን እና አድካሚ ጊዜያት ማሳለፏን በማውሳት፣ በስተመጨረሻ የአልበሙ ስራ ተገባድዶ ለፍሬ በመብቃቱ የተሰማትን ደስታ ገልጻለች።

“አልበሙን የሰሙ ሁሉ እንደሚወዱት ተስፋ አደርጋለሁ” ያለችው ድምጻዊት ሄለን በርሄ፣ አልበሙ በ”Helen Berhe Official” የዩቲዩብ ገጽ እና በሌሎች የሙዚቃ ማሰራጫ አማራጮች ለአድማጮች ተለቋል።

“የበረታ” የሙዚቃ አልበም በውስጡ አስር ትራኮች ሲኖሩት፣ በሙዚቃ ቅንብር ሱራፌል የሺጥላ፣ አብርሃም ኪዳኔ እና ፋኑኤል አሰፋ ተሳትፈዋል። በአልበሙ ላይ ሐዲስ ዓለማየሁ (ሐዲንቆ)፣ አማኑኤል ወርቁ፣ አቤል ዓለማየሁ፣ በረከት ባዩን ጨምሮ በርካታ ባለሞያዎች በቀጥታ የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎችን በመጫወት አሻራቸውን አሳርፈዋል።

የግጥም እና ዜማ ድርሰት ላይ ኢዮቤል ብርሃኑ፣ ድምጻዊቷ ሄለን በርሄ፣ ታደሰ ገለታ፣ ምሕረትአብ ደስታ፣ ዘርአብሩክ ሰማው፣ ሱራፌል የሺጥላ እና ከድር አሊ ተጠብበውበታል። በሚክሲንግ እና ማስተሪንግ ሰለሞን ሃይለማርያም፣ ፋኑ ጊዳቦ እና አብርሃም ኪዳኔ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።

ድምጻዊት ሄለን በርሄ በቅርብ ጊዜ በኦሮምኛ ቋንቋ በሰራችው ሙዚቃ የኦዳ ሽልማት ተሸላሚ እንደነበረች የሚታወስ ነው።





1 comment

Leave a Comment