banner

ከ70 በላይ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የባህልና ቱሪዝም ዘመቻ ይፋ ተደረገ!

#Fastmereja:-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚገኙ ሁለንተናዊ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና የተፈጥሮ ሀብቶችን ለሀገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ ተመልካቾች የሚያስተዋውቅ ታላቅ የኪነ-ጥበብ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

ፕሮጀክቱ ይፋ የተደረገው የይበልጣል ተረፈ ፊልም ፕሮዳክሽን እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሙዚቀኞች ማህበር በዛሬዉ እለት በሳፋየር አዲስ ሆቴል በተካሄደው የፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ የመግባቢያ ስምምነት ባደረጉበት ወቅት ነው።

የፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ የይበልጣል ተረፈ ፊልም ፕሮዳክሽን ተወካይ አቶ ፍፁም ሚሊዮን እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዝዳንት አርቲስት ወንድሙ ከበደ (ዳውሮ ባና) ተገኝተው ሰነዱን ተለዋውጠዋል።

ከፍተኛ በጀትና ዝግጅት የሚጠይቀው ይህ ዘመቻ በክልሉ በሚገኙ ስድስት ዞኖች (ከፋ ዞን፣ ሸካ ዞን፣ ቤንች ሸኮ ዞን፣ ምዕራብ ኦሞ ዞን ፣ ዳውሮ ዞን እና ኮንታ ዞን) እንዲሁም በአራት የከተማ አስተዳደሮች ላይ ቀረጻውን እንደሚያካሂድ ተገልጿል።

ለዚሁ ስራ ከአዲስ አበባ የሚጓዙ ከ70 በላይ አንጋፋና ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች እና የሚዲያ አካላት የሚሳተፉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አርቲስት ሚካኤል ታምሬ፣ ድምፃዊት ሃሊማ አብዱራሃማን፣ አርቲስት ሙላለም ጌታቸው፣ ድምፃዊት ዘቢባ ግርማ፣ ካሳሁን ፍስሃ (ማንዴላ)፣ ፋንታ ስንታየሁ፣ ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው፣ ኢየሩሳለም ገበየሁ እና ምትኩ በቀለ እንደሚገኙበት ነዉ የተገለፀዉ።

ተሳታፊ አርቲስቶቹ በስድስት ቡድን ተከፍለው እያንዳንዱን ዞን በመወከል ከማህበረሰቡ ጋር አብረው በመኖርና በመወያየት እውነተኛውን የክልሉን ህይወት የሚያንጸባርቁ የሲኒማና የሙዚቃ ስራዎችን እንደሚያዘጋጁም ተገልጿል።

የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ የ13ቱን ብሔረሰቦች ባህላዊ ብዝሃነት፣ የተፈጥሮ ሀብቶችና የቱሪዝም መስህቦችን በዘመናዊ የሲኒማ ቴክኖሎጂ አስደግፎ ማስተዋወቅ ሲሆን በተጨማሪም አዳዲስ የኢንቨስትመንት እድሎችን ወደ ክልሉ መሳብ፣ ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እና የወል ትርክት ግንባታን ማጠናከር የዚሁ ጥረት አካል እንደሆነ ተገልጿል።

በፊልም፣ በሙዚቃ፣ በዶክመንተሪ እና በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች መልክ የሚዘጋጀው ይህ ልዩ የኪነ-ጥበብና የመዝናኛ ፕሮግራም፣ በዚሁ ዓመት በገና በዓል ዕለት በሁሉም የማሰራጫ አማራጮች ለተመልካች እንደሚቀርብ ታዉቋል።





Leave a Comment