#Fastmereja:-በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የትዳር መፍረስ እና የፍቺ መጠን ለመቀነስ የሚያስችል አዲስ የትምህርት፣ የስልጠና እና የምክር አገልግሎት መርሃ-ግብር ይፋ መደረጉን ዳሚና (Damiina) በዛሬዉ እለት አስታዉቋል።
የትዳር እና የግንኙነት አማካሪ እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት አቶ ኢብሳ መሀመድ(ዳሚና) ”ቁርስ ከዳሚና ጋር” (Breakfast with Damiina) በሚል ስያሜ ይፋ ያደረገው ይህ መርሃ-ግብር፤ አዲስ ተጋቢዎችን፣ ባለትዳሮችን፣ በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ያሉትን እንዲሁም ለትዳር ህይወት ዝግጅት የሚያደርጉ ወጣቶችን ያካተተ ተግባራዊ የስልጠና መድረክ መሆኑ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከ20 ሺህ በላይ ፍቺዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከ5 ሺህ በላይ የትዳር ፍቺዎች ተመዝግበዋል።
ይህ አሃዝ በትዳር እና በፍቅር ግንኙነቶች መካከል ያሉ ፈተናዎችን በግንዛቤ፣ በትምህርት እና በባለሙያ ድጋፍ መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል ተብሏል።
ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመስጠት የተዘጋጀው የዳሚና ጥረት፤ በመጀመሪያው ዙር በአንድ ቀን ስልጠና ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን እና ጥንዶችን ተዳራሽ ለማድረግ የተነሳ መሆኑም ነዉ የተገለፀዉ።
ስልጠናው በዋናነት፦ ውጤታማ መግባባት እና የጋራ ግንዛቤ፣ስሜታዊ ንቃተ-ህሊና (Emotional Awareness)፣ የቅራኔ አፈታት ስልቶች፣የትዳር እና የግንኙነት ኃላፊነቶች፣ዘላቂ አጋርነትን መገንባት በሚሉ ቁልፍ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩርም ነዉ የተገለፀዉ።
መርሃ-ግብሩ ግንኙነቶች ወደ መፍረስ ደረጃ እስኪደርሱ ከመጠበቅ ይልቅ፣ ገና ከጅምሩ ጤናማ እና ዘላቂ ግንኙነትን ለመገንባት የሚያስችሉ እውቀቶችና ክህሎቶችን አስቀድሞ በማስጨበጥ ላይ ትኩረት ያደርጋልም ተብሏል።




