banner

አዋሽ ኢንሹራንስ በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ላይ የተመዘገበ የመጀመሪያው ኩባንያ መሆን ቻለ!

#Fastmereja:- አዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ. በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ (ESX) ዋና ገበያ ላይ በይፋ በመመዝገብ፣ በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ ታሪክ የመጀመሪያው የኢንሹራንስ ኩባንያ በመሆን የምዝገባ ማረጋገጫ የዕውቅና ሰርተፍኬት በዛሬዉ እለት በተካሄደ መርሀ-ግብር ተበርክቶለታል።

ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ የተከናወነው በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን በኩል አስፈለጊው የምዝገባ ሂደት በስኬት ከተጠናቀቀ እና አክሲዮኖቹ በብሔራዊ ባንክ ማዕከላዊ የኤሌክትሮኒክ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግምጃ ቤት ከተካተቱ በኋላ መሆኑ ታውቋል።

በምዝገባው ሂደት አዋሽ ኢንሹራንስ “AWIN” የሚል የምልክት ስም (Ticker Symbol) የተሰጠው ሲሆን፣ በድምሩ 6,750,604 አክሲዮኖችን በዋናው ገበያ በማስመዝገብ ነዉ የተቀላቀለዉ።

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዮዲት ካሳ እንዳስታወቁት፤ የመጀመሪያውን የኢንሹራንስ ኩባንያ በዋናው ገበያ መቀበል የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እየሰፋና እየጠለቀ መምጣቱን እንደሚያሳይ ገልፀዉ የኢንሹራንስ ተቋማት ስጋትን የሚያስተዳድሩና የረጅም ጊዜ ቁጠባን የሚያሰባስቡ በመሆናቸው፣ በገበያው ላይ መገኘታቸው ለኢንቨስተሮች አዲስ የኢንቨስትመንት ዕድል እንደሚከፍት አስገንዝበዋል።

እንዲሁም የአዋሽ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጅባት አለምነህ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዋለ ንዋዮች ገበያ ላይ መመዝገብ ለተቋማዊ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት እና ለባለአክሲዮኖች ዘላቂ እሴት ለመፍጠር የሚያስችል አዲስ የዕድገት ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ታሪካዊ ምዝገባ ኢንቨሰተሮች በአዋሽ ኢንሹራንስ ዕድገት ውስጥ እንዲሳተፉ አዳዲስ ዕድሎችን የሚፈጥር ሲሆን፣ የኩባንያዉን የአሰራር ግልጸኝነት፣ ጠንካራ ተቋማዊ አስተዳደር እና ተጠያቂነት እንዲሁም ለባለአክሲዮኖች ዘላቂ ዕሴት ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት ያጠናክራል።

እ.ኤ.አ. በ1994 የተመሠረተው አዋሽ ኢንሹራንስ፤ ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ በኢንሹራንስ ዘርፍ ያካበተውን ልምድ በመጠቀም አጠቃላይ፣ የሕይወትና ጤና እንዲሁም የተካፉል ኢንሹራንስ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየ ፈር ቀዳጅ ተቋም ነው፡፡





Leave a Comment