#Fastmereja:- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚገኙ መሰረታዊ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጠቅላላ ሀብታቸው ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን የከተማ አስተዳደሩ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽንና በአዲስ አበባ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ በመሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ78ኛ በከተማችን ደግሞ ለ35ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓመታዊ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ቀን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ህዳር 3 ቀን 2019 ዓ.ም በራስ ሆቴል የምክክር ወርክሾፕ አካሂደዋል።
“የኅብረት ሥራ ፋይናንስ ለተረጋጋ ኢኮኖሚ ዓለም ልዩ ምልክት ናቸው” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ኀብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ መሪማ ደሊል እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ ከ1,106 በላይ መሰረታዊ የቁጠባና ብድር ማኅበራት እና ሁለት ዩኒየኖች ከ291 ሺህ 448 በላይ ግለሰብ አባላትን አቅፈው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። እነዚህ ማኅበራት በአማካይ በየዓመቱ 2.7 ቢሊዮን ብር ብድር የመስጠት አቅም ላይ መድረሳቸውንም አመላክተዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃም በኢትዮጵያ ከ18 ሺህ 500 በላይ የቁጠባና ብድር ማኅበራት ከ8 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በማቀፍ፣ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ የቁጠባና የአክሲዮን ገንዘብ በማሰባሰብ እንዲሁም ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር በማቅረብ ለሀገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተጫኔ አዱኛ በበኩላቸው፣ የዘንድሮው መሪ ቃል ዓለማችን በፈጣን የኢኮኖሚ ለውጥና በፋይናንስ እርግጠኝነት ማጣት ውስጥ በምትገኝበት ወቅት፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በመተማመን፣ በግልጽነትና በጋራ ኃላፊነት ላይ የተመሰረተ የተረጋጋ የፋይናንስ አገልግሎት ለማኅበረሰቡ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረጋቸውን የሚያጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራንና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት በዚህ ወርክሾፕ፣ በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል በአሰራር ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ ውይይቶች ተካሂደዋል።
በተለይም ማኅበራቱን በቴክኖሎጂ በማዘመን፣ ዘመናዊ የሂሳብ አያያዝ ሥርዓት በመዘርጋት እና የአመራር ብቃትን በማሳደግ ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል።




