banner

በሞባይል ስልክ ለተሰሩ ፊልሞች ዕድል የሚሰጠው 21ኛው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ሊካሄድ ነዉ!

#Fastmereja:-ለሃያ አንድ ዓመታት ያለማቋረጥ ሲካሄድ የቆየው ታላቁ የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል፤ ዘንድሮ ከአዲስ ቲያትር እና ሲኒማ እንዲሁም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ በድምቀት እንደሚካሄድ በዛሬዉ እለት በተሰጠ መግለጫ ተገልጿል።

ከህዳር 6 እስከ 13 በሚካሄደዉ በዘንድሮው መርሃ ግብር ከ50 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ፊልሞች ለዕይታ የቀረቡ ሲሆን፤ ተመልካቾች በቴሌብር የ50 ብር ትኬት ብቻ በመግዛት ሳምንቱን ሙሉ ፊልሞቹን መመልከት የሚችሉበት «በ50 ብር 50 ፊልሞች» የተባለ ልዩ የቅናሽ ዕድል መዘጋጀቱ ተነግሯል።

ይህንን ታላቅ ዓመታዊ ፌስቲቫል አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የፌስቲቫሉ መስራችና አዘጋጅ አቶ ይርጋሸዋ ተሾመ፤ ቀደም ባሉት ዓመታት አጋጥመው የነበሩ የፋይናንስ እና የመድረክ እጥረት ፈተናዎች ዘንድሮ ከአዲስ ቲያትር እና ሲኒማ፣ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በተደረገ የጠበቀ ጥምረት ሊቀረፉ መቻላቸውን ገልጸዋል።

የዘንድሮውን ፌስቲቫል ከዚህ ቀደሞቹ ለየት ከሚያደርጉት አዳዲስ ምዕራፎች መካከል በሞባይል ስልክ ብቻ የተሰሩ ፊልሞች የሚወዳደሩበት አዲስ ዘርፍ መጀመሩ የተገለፀ ሲሆን ይህም ዩቲዩበሮች እና ቲክቶከሮች በስልካቸው የቀረጹትን የፈጠራ ስራ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ አቅርበው እንዲወዳደሩ ሰፊ ዕድል የከፈተ መሆኑ ተመላክቷል።

ከዚህም ባሻገር ከሩሲያ፣ ከቻይና፣ ከአሜሪካ እና ከካናዳ የፊልም ተቋማት ጋር በተደረጉ ስምምነቶች መሰረት የፊልም ፓናል ልውውጥና የውይይት መድረኮች የሚካሄዱ ሲሆን በዚህም ከአሜሪካ የመጡት የ«Black Slaughter» ፊልም ባለሙያዎችና የ«Russian Days> ተሳታፊዎች ጠቃሚ ልምዶቻቸውን ለሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ያካፍላሉ ተብሏል።

በመግለጫው ላይ የተገኙት የአዲስ ቲያትር እና ሲኒማ ምክትል ኃላፊ አቶ ፍቅሬእየሱስ አብርሃም በበኩላቸው፤ መንግስት ለኪነ-ጥበብ ዘርፉ በሰጠው ትኩረት ዘመናዊ ሲኒማ ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅሰው፣ የጥበብ ባለሙያዎች በጋራ በመሆን የሀገርን መልካም ገጽታ የሚገነቡ ታላላቅ ስራዎችን እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል፣ የዲቦራ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ቤኪ አባዱላ ፋውንዴሽኑ ከሩሲያው «RT Media» ጋር በመተባበር «Inspired by Deborah» የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ለዕይታ ማብቃቱንና በጉዳዩ ላይ ውይይት መደረጉን አስታዉሰዉ ዘጋቢ ፊልሙ ዳውን ሲንድሮም እና የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ህጻናት በትምህርት፣ በጤና እና በስራ እድል ለማብቃት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን የሚያሳይና የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

የፌስቲቫሉ የመክፈቻና የመዝጊያ ስነ-ስርዓቶች ለተመልካች በነጻ ክፍት የሚደረጉ ሲሆን፤ እሁድ ከ11 ሰዓት ጀምሮ በሚከናወነው የመዝጊያ መርሃ ግብር በ12 ዘርፎች አሸናፊ ለሆኑ የኢትዮጵያ ፊልም ባለሙያዎች ሽልማት እንደሚበረከት ተገልፆ አሸናፊ የሚሆኑት ፊልሞችም በቀጣይ በቻይና እና በካናዳ በሚዘጋጁ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫሎች ላይ እንዲቀርቡ እንደሚደረግ ነዉ የተገለፀዉ።





Leave a Comment