#Fastmereja:- በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የካፒታል ገበያ የሚቀላቀለው ኤ.ኤም.ጂ (AMG) ኢንቨስትመንት ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን (ECMA) የሥራ ፈቃዱን በዛሬዉ እለት በይፋ ተረክቧል።
በ50.1 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተው ይህ ተቋም፣ በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ቢሮ በተካሄደ ደማቅ ሥነ-ሥርዓት ላይ ፈቃዱን የተረከበ ሲሆን፣ ለመንግሥትና ለግል ተቋማት እንዲሁም ለግለሰብ ባለሀብቶች የተሟላ የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሃና ተኸል እንደገለፁት፣ እስካሁን ከባንኮች ጋር የተቆራኙ ዘጠኝ የኢንቨስትመንት ባንኮች ፈቃድ ማግኘታቸውን ገልጸው፣ ከግል ዘርፉ የወጡ ልምድ ያላቸው ተቋማት መቀላቀላቸው ገበያውን ለማስፋት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው እና አዳዲሶቹ ተቋማትም ታማኝነትንና ግልጽነትን መሠረት በማድረግ ገበያውን እንዲያሳድጉ አሳስበዋል።
እንዲሁም የኤ.ኤም.ጂ ኢንቨስትመንት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበራ በቀለ ቀጄላ በበኩላቸው፣ ተቋሙ በዋናነት በካፒታል ማሰባሰብ የማማከር ሥራ እና በገበያው ላይ የገንዘብ ፍሰትን (Liquidity) በማሳደግ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
ባንኩ ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች መካከል የአክሲዮንና የቦንድ ሽያጭ (IPO)፣ ኢስላሚክ ፋይናንስ (ሱኩክ)፣ የውህደትና ግዢ (M&A) ምክር፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ደላላነት (Brokerage) እንዲሁም ወደ ግል የሚዛወሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ሂደት ማገዝ ይገኙበታል።
በተጨማሪ ከፋይናንስ፣ ከማኑፋክቸሪንግና ከግብርና ማቀነባበሪያ ባለፈ በቴክኖሎጂ (ፊንቴክ፣ ሄልዝቴክ፣ አግሪቴክ) እና በአረንጓዴ ፋይናንስ ዘርፎች ላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ የገለጸው ኤ.ኤም.ጂ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ በቀጣይ የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ (ESX) አባል በመሆን ዲጂታል የግብይት አማራጮችን ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዱም ነዉ የተገለፀዉ።
ይህም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ወጣቶች በአነስተኛ ገንዘብ ጭምር በቀላሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በር የሚከፍት እንደሆነም ተገልጿል።



