banner

ያንጎ ግሩፕ በአዲስ አበባ ከ12,500 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የመንገድ ደኅንነት ሥልጠና ሰጠ

#FastMereja I መቀመጫውን በዱባይ ያደረገው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ያንጎ ግሩፕ፣ በመላው አፍሪካ እየተገበረ ያለውን “ደኅንነቱ የተጠበቀ የትምህርት ቤት ጉዞ” (Safer Journeys to School) የተሰኘውን ተነሣሽነት ወደ ኢትዮጵያ በማስፋፋት በአዲስ አበባ ለሚገኙ ከ12,500 በላይ ተማሪዎች የመንገድ ደኅንነት ሥልጠና መስጠቱን ኩባንያው አስታውቋል። ኅዳር 05 ቀን 2019 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው ይህ መርሐ ግብር ከሴቭ ዘ ኔሽን (STN) እና ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የተከናወነ ሲሆን፣ በመዲናዋ በሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሕጻናት በትራፊክ ፍሰት ውስጥ ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲንቀሳቀሱ ለማገዝ ለ25 ቀናት የቆየ ተግባራዊ ሥልጠና ተሰጥቷል።

ፕሮግራሙ ከክፍል ውስጥ ትምህርት ባሻገር በሁለት ትምህርት ቤቶች አካባቢ የመንገድ ደኅንነት ሁኔታ ግምገማ በማካሄድ የእግረኞች መሻገሪያዎችን፣ የፍጥነት መቀነሻ ጉብታዎችን፣ የፍጥነት ገደብ ምልክቶችን እና መከላከያ አጥሮችን የመገንባት የመሠረተ ልማት ማሻሻያ ሥራዎችን አከናውኗል። በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ የመንግሥት ኃላፊዎች ተነሣሽነቱ መንግሥት ከያዘው የመንገድ ደኅንነት ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣምና ለትራፊክ ባለሙያዎችም ጠቃሚ ተሞክሮ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው፣ የሕጻናትን ደኅንነት ለመጠበቅ ለተደረገው አስተዋጽኦ ያንጎንና አጋር አካላትን አመስግነዋል።

የያንጎ የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር የቀናለም አበበ በበኩላቸው፣ ደኅንነት ለያንጎ ሁሌም ከፍተኛ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኩባንያው ከቴክኖሎጂ አገልግሎቶቹ ባሻገር ሕጻናት በየዕለቱ ወደ ትምህርት ቤት ሲጓዙ በራስ መተማመንና ደኅንነት እንዲኖራቸው እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። የሴቭ ዘ ኔሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ምስጋናው ቢምረውም፣ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ21,000 በላይ ሰዎች በመንገድ አደጋ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ እንደሚያሳይ በመጥቀስ፣ በትምህርት ቤቶች በተቋቋሙ የደኅንነት ኮሚቴዎችና ክበባት አማካኝነት ሥራው በዘላቂነት እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም በዛምቢያና በሴኔጋል ከ34,000 በላይ ሕጻናትን ተጠቃሚ ያደረገው ይህ ተነሣሽነት፣ ያንጎ ግሩፕ በሚንቀሳቀስባቸው ማኅበረሰቦች ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር ከሚያከናውናቸው ፕሮግራሞች አንዱ ነው። ኩባንያው በኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመተባበር የደም ልገሳ መርሐ ግብር ማካሄዱን፣ በ“Yango Cares” አማካኝነት ለአጋር አሽከርካሪዎች ድጋፍ ማድረጉን እንዲሁም በያንጎ ፌሎውሺፕ ፕሮግራም በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስናና ሒሳብ (STEM) ዘርፎች ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች እየደገፈ እንደሚገኝ በመግለጫው ተመልክቷል።





Leave a Comment