#Fastmereja:-ፈጥኖ ደራሽ ማይክሮፋይናንስ ተቋም አ.ማ. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የንግድ እና የሥራ ጅምር ፈቃድ በማግኘት የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በዛሬዉ እለት በልኳንዳ ተራ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመርቆ ወደ ስራ ገብቷል።
በ820 መሥራች ባለአክሲዮኖች የተቋቋመው ተቋሙ፤ 238 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የተፈረመ እና 93 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ ወደ ፋይናንስ ገበያው ተቀላቅሏል።
ተቋሙ በተሻሻለው የማይክሮፋይናንስ ሥራ አዋጅ ቁጥር 626/2009 መሠረት የተቋቋመ ሲሆን፣ ሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. የንግድ ፈቃድ እንዲሁም መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም. የሥራ ጅምር ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ ማግኘቱ ተገልጿል።
ስያሜውን በ1947 ዓ.ም. ከተመሠረተው ታሪካዊው የ«ፈጥኖ ደራሽ» ፖሊስ ካምፕና አካባቢ ያገኘው ይህ ተቋም፣ የአካባቢው ወጣቶች፣ ቤተሰቦች እና የልማት ወዳጆች ባደረጉት ጥረት እውን መሆኑ ተመላክቷል።
በዛሬው ዕለት በተካሄደው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌታቸው ይመር፣ የዘመን ባንክ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ኢንጂነር ቢጂአይ ናይከር እና የአቢሲኒያ ባንክ አይ.ቢ.ዲ ዳይሬክተርን ጨምሮ የቦርድ አባላት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም ከ500 በላይ ባለአክሲዮኖች ተገኝተዋል።
«ፋይናንስን በፈገግታ!» በሚል መሪ ቃል ሥራውን የጀመረው ፈጥኖ ደራሽ ማይክሮፋይናንስ፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች ከባንክ አገልግሎት ውጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለመሆን ያለመ ስለመሆኑም ነዉ የተገለፀዉ።
ተቋሙ ከመደበኛውና ወለድ አልባ የቁጠባ አማራጮች ባሻገር፤ ባህላዊውን እቁብ ከዘመናዊ ቁጠባ ጋር ያጣመረ «የተማሪዎችና የማኅበረሰብ እቁብ ቁጠባ» እንዲሁም መነሻ ካፒታል ለሌላቸው ወጣቶች በማኅበረሰባዊ ዋስትና ብድር የሚያቀርብበትን የ«ሃሳብ ፋይናንሲንግ» (Idea Financing) አሠራር ይዞ መቅረቡን አስታውቋል።
በተጨማሪም ለሴቶች፣ ለወጣቶች፣ ለግብርና ዘርፍ እና ለጥቃቅንና አነስተኛ ንግዶች የተቀላጠፈ ብድርና የንግድ ሥልጠና ድጋፍ በመስጠት እስከ 2030 ዓ.ም. ድረስ በሀገሪቱ ተወዳዳሪ የፋይናንስ ተቋም ለመሆን እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።




