በኢትዮጵያ እስከ አሁን ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ለመውሰድ መመዝገባቸውን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የዲጅታል መታወቂያ አገልግሎት “አንድ ሰው አንድ ነው” የሚለውን መርህ ይዞ የግለሰቦችን መረጃ በመሰብሰብ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር እየተካሄደ ይገኛል።
የምዝገባ ሂደቱም እስከ አሁን በቅንጅትና በተሳለጠ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የተቋማት ተሳትፎ አማካሪ ኦላና አበበ ገልጸዋል።
የዲጅታል መታወቂያ አገልግሎት ሀገራዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑን የተናገሩት አማካሪው የዲሞግራፊክና ባዮሜትሪክ መረጃን መዝግቦ በማዕከላዊ ቋት በመያዝ ለእያንዳንዱ ነዋሪ ልዩ ቁጥር መስጠት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በፕሮጀክቱ በቀጣይ ሦስት ዓመታት 90 ሚሊየን ዜጎችን የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን አስታውሰው እስካሁን ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ለመውሰድ መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ለሦስት ዓመታት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከባንኮች፣ ከገቢዎችና የወሳኝ ኩነት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት በፋይናንስ ዘርፍ መተግበር በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ግልጽነትን እና አካታችነትን በማጎልበት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል ሲል አዲስ ዋልታ ነው የዘገበው።