#FastMereja
በተለያዩ ወንጀሎች ጥርጣሬ ተከስሰዉ የታሰሩት የቀድሞ የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደዓ በዋስ እንዲለቀቁ ያቀረቡት አቤቱታ ዛሬም ዉሳኔ አላገኘም። ባለፈዉ ሐምሌ 30፣ 2016 አዲስ አበባ ያስቻለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግስትና ሕገ-መንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት አቶ ታዬ ላይ ከተመሠረተባቸዉ ሶስት ክሶች ከሁለቱ በነጻ አሰናብቷቸዉ ነበር።
ይሁንና ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ ይዘው ተገኝተዋል በሚል የቀረበባቸውን 3ኛ ክስ ግን እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ በይኖ ነበር፡፡ የአቶ ታዬ ባለቤት ወይዘሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት አቶ ታዬ ሥስተኛዉን ክስ በዋስ ተለቅቀዉ እንዲከራከሩ ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤት ዉድቅ አድርጎባቸዋል። በዚሕም ምክንያት ተከሳሹ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ይግባኝ ጠይቀዉ ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቷቸዉ ነበር።
ወይዘሮ ስንታየሁ እንዳሉት ፍርድ ቤቱ አቤቱታን ዛሬ ማየት አልቻለም። አቶ ታዬ ደንደዓ የተመሰረተባቸዉን ክስ ያለጠበቃ በራሳቸዉ እየተከራከሩ ነዉ። የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ስዩም ጌቱ እንደዘገበዉ አቶ ታዬ የጥብቅና መብት ለመከልከላቸው መንግስትን ተጠያቂ አድርገው፣ የብሔራዊ መረጃ ደህንነት ያሉትን ተቋም መክሰሳቸው አይዘነጋም፡፡ አቶ ታዬ የገዢዉ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ የኦሮሚያ ምክር ቤት አባልና ሚንስትር ደ ኤታ ነበሩ ሲል ዶቼ ቬለ በዘገባው ጠቁሟል።

1 comment
ስንት ነፍሰ ገዳይ እየተለቀቀ አይደል እንዴ🙄 ይሄን ያህል ምን አድርጎ ነው 🙄 ቢያንስ ከዚህ ቀደም ስለሰራቸው መልካም ስራዎች ተብሎ በዚህ ልክ ባይጨከንበት !!!