banner

ያጉት ፔይ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ከኢትስዊች ጋር የፋይናሺያል አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስምምነት ተደረገ።

#FastMereja
ያጉት ፔይ ፋይናንሺል ቴክኖሎጂ እና አክሲዮን ማህበር ከኢትስዊች ጋር ባደረገው የፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ጥምረት አገልግሎት መስጠት ሊጀምር መሆኑን በዛሬው እለት በሸራተን አዲስ ሆቴል ተቋማቱ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ አሳወቁ።

ያጉት ፔይ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ከኢትስዊች ጋር ባደረገው ጥምረት በድርጅቱ ፖስ ማሽኖች ላይ ተናባቢ የካርድ ክፍያ አገልግሎትን ለመተግበር የሚያስችል የአጋርነት ስምምነት በመፈራረም በሁለቱ ተቋማት መካከል የፋይናንስ ቴክኖሎጂዎችን የማስተሳሰር ስራ ተፈፅሞ ወደ ሙከራ ትግበራ መግባቱን ተቋመቱ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።

የኢትስዊች ቺፍ ኦፕሬሽን ኦፊሰር አቶ ነቢዩ መንግስቱ እንደገለጹት “ኢትስዊች በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ተጠቃሚነትን በሚያበረታቱ ጅምሮች ላይ ግንባር ቀደም መሆኑን ገልጸው ያጉት ፔይን ከኢትስዊች ጋር ለማስተሳሰር የተደረገው የትግበራ ሂደትም ውጤታማ ሆኗል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም “ኢትስዊች ኢትዮጵያ ለተለመችው የዲጂታል የክፍያ ስርዓት ግንባታ አስፈላጊውን የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት እያቀረበ ይገኛል፡፡ ሁሉም የክፍያ አገልግሎት አቅራቢ የፋይናንስ ተቋማትም በኢትስዊች አማካኝነት አገልግሎታቸውን ተደራሽ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የያጉት ፔይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተሾመ አለማየሁ በበኩላቸው “ያጉት ፔይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የክፍያ ኦፕሬተር ፈቃድ በማግኘት 1000 የክፍያ ነቁጥ (POS) ማሽኖችን ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ በተመረጡ የግብይት ማእከላት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

ስለሆነም የማንኛውም የሀገር ውስጥ ባንኮች የክፍያ ካርድ ተጠቃሚ ደንበኞች በነዚህ የግብይት ማዕከላት በሚገኙ የድርጅቱ ፖስ ማሽኖች ክፍያቸውን መፈፀም የሚያስችላቸውን የኔትዎርክ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አጠናቋል” ብለዋል፡፡

ያጉት ፔይ በኢትዮጲያ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የተሳለጠ የክፍያ አገልግሎት ስርአት ያበለፀገ በመሆኑ በዲጂታል ክፍያ ኦፕሬተር ስራ በሀገራችን አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ፈር ቀዳጅ ተቋም ያደርገዋል። በቀጣይም ዘርፈ ብዙ አዳዲስ የቴክሎኖጂ አማራጮችን በማቅረብ ለሃገራችን የዲጂታል ክፍያ ስርአት መጎልበት የሚያደርገው አስተዋፅኦ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ኢትስዊች አማ.ሃገራችን ውስጥ ባሉ በሁሉም የግል እና የመንግስት ባንኮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ የተቋቋመ ብሔራዊ ስዊች ሲሆን በቅርቡ ደግሞ የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት፣ የክፍያ ስርዓት ኦፕተሮች እና የክፍያ መፈፀሚያ ሰነድ አውጪዎች በባለቤትነት ተቀላቅለውታል፡፡

ዋና አላማውም በፋይናንስ ተቋማት መካከል በዲጂታል አማካኝነት የሚደረጉ ግብይቶችን/ክፍያዎችን ተናባቢ ማድረግ፣ የሀገር ውስጥ የክፍያ ስርዓትን ማቅረብ፣ የብሔራዊ ክፍያ ጌትዌይ አገልግሎትን መስጠት፣ ለዲጂታል ክፍያዎች የመጨረሻ ሒሳብ የማጣራት እና የማወራረድ የማዕከላዊ አገልግሎት መስጠት እና ለፋይናንስ ተቋማት የጋራ መሰረተ ልማት እና ሲስተሞች ማቅረብ ናቸው፡፡





Leave a Comment