banner

«ዕርቁ የማያስደስተው ሰይጣንን ብቻ ነው»

አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ በደራርቱና በገዛኸኝ አበራ ዕርቅ ዙሪያ በተለይ ለሀትሪክ ስፖርት ይስሀቅ በላይ

👉የደሬና የገዛኸኝ ዕርቅ የጠወለገ አበባ ዳግም ነፍስ ዘርቶ ሲፈካ የማየት ያህል ነው

👉ዕርቁ የማያስደስተው ሰይጣንን ብቻ ነው

👉እኔና ደራርቱ ልብ ለልብ እንተዋወቃለን፤የሁለታችንን ፀብ ይመኙታል እንጂ አያገኙትም

👉እኔም ገዛኸኝም፣ደሩም ሌላውም የምንቆመው ከግለሠብ ጋር ሳይሆን ነጭ ላባችንን ካፈሰስንለት፣ከደማንለት አትሌቲክስ ጋር ብቻ ነው

👉ደሩ ከእኛ በተቃራኒ ቆማለች ብለህ እንዳታስብ፤የደማችለትን፣ነጭ ላቧን ያፈሠሰችለትን፣ያለቀሠችለትን አትሌቲክስ በተቃራኒ ቆማ ትጎዳለች ብለህ ካሠብክ በጣም የዋህ ሠው ነህ

👉የስፖርቱን መንደር ሠላም የሚያደፈርሱ ነገሮች በደሩና በገዛኸኝ መንገድ ቢፈቱ የመጀመሪያ ምርጫዬ ነው

ባለፈው ዓርብ ለብዙዎች ጭንቀት መፍትሄ የሆነ በጎ ተግባር በኃይሌ ግራንድ ሆቴል ተፈፅሟል፤በመካከላቸው ንፋስ ገብቶ ለወራቶች ተኮራርፈው የቆዩትን ሁለቱን የአትሌቲክስ ጀግኖቻችንን ረዳት ከሚሽነር ደራርቱ ቱሉንና አትሌት ገዛኸኝ አበራን ከልዩነት ወደአንድነት ያመጣ የዕርቅ ስነ-ስርዓት ተፈፅሟል።ከዚህ በኃላ በደራርቱና በገዛኸኝ አበራ መካከል የፀብ ግድግዳ ተደርምሶ የፍቅር ድልድይ ተገንብቷል፤ምስጋና ለአስታራቂ ሽማግሌዎች ይሁንና ሁለቱ ጀግኖቻችን ቤተሠብነታቸውን፤ፍቅራቸውን አድሠዋል።

የሁለቱ ፀብ እንቅልፍ የነሳው ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ለዕርቁ የእኔ ሚና ኢምንት ነው የደከሙት ሌሎች ናቸው ቢልም ችግሩ እንዲፈታ ትልቁን ሚና ተጫውቷል፤በዕርቁ ስነ-ስርዓት ላይ ሀይሌና ደራርቱ ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው እንባቸውን ያፈሠሱበት ፕሮግራም ፍፃሜው ሠላምና አንድነት ሆኗል፤ ፡ከዕርቁ በኃላ ከሠጠመበት የደስታ ባህር ውስጥ ሳይወጣ የሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያሉ ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ አነጋግሮት በዚህ መልኩ አጠናክሮታል።

.🎤..እርቁ ስለፈጠረበት ስሜት…

✍”…ኡ በጣም ነው የተደሠትኩት ምን ልበልህ የሆነ የጠወለገ አበባ ዳግም ነፍስ ዘርቶ ሲፈካ አይተህ ታውቃለህ?ልክ እንደዛ በሁለቱ ጀግኖች አትሌቶች መካከል በተፈጠረ ልዩነት ጠውልገው የነበሩ ነገሮች በሙሉ የፈኩበትና ያማሩበት ነገር ነው የተፈጠረው፤በእርቁ ወቅት የነበረው ስሜት ልብ የሚነካ ነበር…ልክ ከ20 እና 30 ዓመት በፊት ወደነበረን ፍቅርና ትዝታ ነው የመለሠን…፤…የነበረው ክፍተት የብዙዎችን ሞራል የሠበረ፣ብዙዎችን ኢትዮጵያዊያንን ያስጨነቀ ነበር፤አሁን ግን የሚሊዮኖችን ሞራል የሚጠግን ነው…”

🎤…የሁለቱ ጀግና አትሌቶች ፀብ አትሌቲክሱ ላይ ስለጣለው መጥፎ ጥላ…

✍”…ምን ጥያቄ አለው መጥፎ ጥላ ነበር ያሳረፈበት፤ሁለቱ አትሌቶች የሀገር ምልክቶች ባለታሪኮች ናቸው፤ህዝቡ እንደአይኑ ብሌን የሚያየው አትሌቲክስ መሪዎች ናቸው፤ለብዙ ወጣቶች መነሳሳትን የሚፈጥሩ፣አትሌቲክሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም መስክ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣መሪዎች እንዲሁም በህዝቡ በጣም የሚወደዱ ናቸው፤በዚህ ልክ የሚታዩ ጀግኖች መካከል ንፋስ ሲገባ ችግሩ እነሱጋ ብቻ አይቆምም፤የአትሌቲክሱንም መንደር ይረብሸዋል፣የህዝቡንም ሠላም ይነጥቃል፤በዕርቁ ሚሊዮኖች እንዴት በደስታ እንደሚቦርቁ ልነግርህ አልችልም፤በተለይ እነሱን እንደሞዴል የሚያያቸው አትሌቶች የተሠበረው ጎናቸው እንዴት እንደሚጠገን ልነግርህ አልችልም…”

🎤…ዕርቁ እንዲፈፀም ኃይሌ ሚናው ከፍተኛ ነው ስለመባሉ…

✍”…ከቀድሞው አትሌት ወርቁ ቢቂላ አንፃር የእኔን ስትመዝነው ኢምንት ነው፤ወርቁ ቢቂላ ይሄ ዕርቅ ዕውን እንዲሆን በጣም ብዙ ደክሟል፤በግሉ ኃላፊነቱን ወስዶ አባገዳዎችና አባሙዳዎችን እንዲሁም ታላላቅ የአትሌቲክሱን ሠዎች እነ ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሸቦ፣አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ፣አሠልጣኝ ቶሌራ ዲንቃን፣አቶ ታምራትና አቶ ኢሳያስ ጅራን አስተባብሮ ለማስታረቅ ደክሞ በመጨረሻ ተሳክቶለታል፤ከዚህ አንፃር የወርቁ ሚና ከፍተኛ ነው እኔ ሆቴሌን ሆቴላችሁ ነው እንኳን ለዚህ ለተቀደሠ ተግባርማ እንደልባችሁ ተጠቀሙበት ከማለት ትንሽ አስተዋፅኦ ከማድረግ የዘለለ ሚና የለኝምና ክሬዲቱን ከእኔ ይልቅ ፈጣሪ፣ወርቁ ቢቂላና ለዕርቁ የተረባረቡት አባገዳዎች፣
አሠልጣኞችና ታላላቅ ሠዎች ቢወስዱ ይሻለኛል፤ወርቁ ቢቂላወንድማችን ቢሆንም ከዚህ በኃላ የሁላችንም ትልቁ ሽማግሌያችን አስታራቂያችን መሆኑን እንድታውቁልን ነው የምፈልገው፤.አስታራቂ አይጥፋ አይደል የሚባለው…”

🎤…ዕርቁ ላይ ትልቅ ሚና ስለተጫወቱት አባገዳና አባሙዳ…

✍”…የተከበሩ አባገዳ ጎበናና የተከበሩ አባሙዳ በሁለቱ ጀግኖች መካከል ሠላም እንዲወርድ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፤ደሬ ቤትም በመሄድ ገዛኸኝንም ለብቻው በማናገርና በመቀጣት ጭምር ሠላም እንዲወርድ አድርገዋል አባገዳ ጎበና በበዓል ምክንያት ባይገኙም በተለይ የተከበሩ አባሙዳ በስነ-ስርዓቱ ላይ የተናገሩት ነገር ልብ የሚነካ ነው፤የደራርቱን እናት ወ/ሮ የሺን ስለጉዳዩ ሲያናግሯቸው እናትዬው ገዛኸኝ ልጄን ምን አርጊ ነው የሚላት?አላሉም[ወይኔ ልጆቼን ምን ገባባቸው?] ነው ያሉት፤ይሄ የሁለቱ ግንኙነት ከጓደኝነት በላይ ያለፈ ቤተሠባዊም እንደሆነ ነው የሚጠቁምህ፤የተከበሩ አባሙዳ ስለእኛ ሲናገሩ ውስጥህ ይረበሻል፤በቃ በጣም ለስፖርት የቀረቡ ናቸው፤[ልጆቼ እናንተን ስናይ ነው ድህነታችንን የምንረሳው፣በእናንተ ነው ሁሉን ረስተን የምንደሠተው፤እናንተ ደግሞ እንቅፋት መታችሁ ሲባል እንኳን እኛ ሙሉ ኢትዮጵያን እንቅፋት እንደመታው ነው የሚቆጠረው]ብለውናልና የነበረው ነገር ስሜትህን ፈንቅሎ ወጥቶ እስከማንባት የሚያደርስ ነው፤እንደዚህ አይነት አርቆ አሳቢ ትልልቅ ሠዎችን አያሳጣን፤የሀገሬ ሠው ምንአለ [ሠማይ ተቀደደ ቢሉት ሽማግሌ ካለ ይሠፋዋል]አለ ይባላል።”

🎤…ብዙዎች በሁለቱ ጀግኖች መካከል ዕርቅ መውረዱን አወድሠው በዚህ አጋጣሚም ኃይሌ ከደራርቱ ቱሉ ጋር ያለውን ልዩነትም ይፍታ የሚሉ ድምፆች ስለመሠማታችው…

✍”…(በጣም እየሳቀ)…ይሄን ጥያቄ ስታነሳ አንድ አባባል አስታወስከኝ [ይመኙታል እንጂ አያገኞትም]ነው የሚባለው…?…ከተሳሳትኩ አርመኝ እንደዛ ነው የምልህ…በሀይሌና ቀደራርቱ መካከል በታሪክ ችግር አይፈጠርም፤እኔና ደራርቱ ልብ ለልብ ነው የምንተዋወቀው፤ብዙ የሚያሴተሳስሩን ታሪኮች አሉ፤እኔና ደሩ ከ1980 ዓ.ም ከአሠላ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ የማውቃት ልጅ ናት፤በአጭሩ ላለፉት 37 አመታት ብዙ ነገሮችን ነው ያሳለፍነው፤የሚገርምህ በዕርቁ ሠዓት እኔም እሷም በቦታው የነበርን ሁሉ በጣም ስሜታዊ ሆነን ነበር፤ከሃያ እና ሰላሳ አመት በፊት ወደነበረው አንድነታችን ነው በትዝታ የተመለስነው፤በአጠቃላይ የዚህ ጥያቄህን መልስ የምዘጋው ከላይ በጠቀስኩልህ፤ይመኙታል እንጂ አያገኛትም በሚለው ነው…”

🎤…ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ከእናንተ በተቃራኒ በመቆም፣ ክስ ከመሠረታችሁባቸው የተከበሩ ዶክተር አሸብር ጎን መቆም ብቻ ሳይሆን ህገወጥ ነው ባላችሁት ምርጫ በምክትል ፕሬዝዳንትነት የተመረጠች ናትና ይሄ የአሁኑ ግኑኝነትና ዕርቅ የሃሳብና የአቋም ለውጥ እንድታመጣ ጫና የሚፈጥር ነው…?… ስለመባሉ…

✍”…(በጣም እየሳቀ)…እኔ ልንገርህ ደሩ ከእኛ በተቃራኒ ቆማለች ብለህ እንዳታስብ፤የደማችለትን፣ነጭ ላቧን ያፈሠሰችለትን፣ያለቀሠችለትን አትሌቲክስ በተቃራኒ ቆማ ትጎዳለች ብለህ ካሠብክ በጣም የዋህ ሠው ነህ፤ደሩ በባህሪዋ ሁሉንም ማስደሠት እንጂ ማስከፋት አትወድም፤ እኔ እስከማውቃት ድረስ ሁልጊዜ ለምን?የምትል ሠው ናት፤ደሩ በዛኛው ወገን ቆማለች ከዚህኛው አይደለችም የሚለው ብዙም አያስኬድም፤እኔም ገዛኸኝም፣ደሩም ሌላውም የምንቆመው ከግለሠብ ጋር ሳይሆን ነጭ ላባችንን ካፈሰስንለት፣ከደማንለት አትሌቲክስ ጋር ብቻ ነው፤የምንቆመው ለሚሮጡት፣ለሚለፉት፣ነጭ ላብ ለሚያልባቸው አትሌቶች ነው፤እኛ እኮ በአሁን ሠዓት ቀገንዘብ፣በጊዜ፣በአእምሮ እየከሠርን ነው፤ጠዋት ማታ ጭንቅላታችን ስለገጠመን ችግር እያሠብን ነው፤ትርፋችን ወደቀደመ ከፍታችን ስንመለስ፣ወጣቶቹ ወርቁን፣ብርና ነሐሱን ለሀገራቸው በማምጣት ወደከፍፍታዋ ሲመልሳት የስፖርቱ መንደር ስፖርቱን በሚያውቁ ሠዎች እጅ ሲወድቅ ብቻ ነው፤የዛን ጊዜ እንኳንም አደረግነው እንላለን…”

🎤…የደራርቱና የገዛኸኝ ዕርቅ እንደመልካም ተሞክሮ ተወስዶ በእናንተና በተከበሩ ዶክተር አሸብርና ካቢኔያቸው መካከል ያለው ልዩነት እንዲፈታ የሚጫወተው ሚና ይኖራል…?… በሚል የሚያነሱ ወገኖች ስለመኖራቸው……

✍”…የስፖርቱን መንደር ሠላም የሚያደፈርሱ ነገሮች በደሩና በገዛኸኝ መንገድ ቢፈታ የመጀመሪያ ምርጫዬ ነው፤በጣምም ደስ ይለኝ ነበር፤ሲጀመርም በዚህ መልኩ እንዲፈታም አሳስበን ነበር የትም መሄድ ይችላሉ ነው የተባለው፤በማንአለብኝና ማን ይነቀንቀኛል የሚሉ ካሉ በሚፈታበት መንገድ እንደሚፈታ ነው የሚሠማኝ፤እኛ አሁንም የምንፈልገው ስፖርቱን ነው፣እኛ እያልን ያለነው አትሌቲክሱን አትንኩብን ነው ሌላ ምንም የምንፈልገው ነገር የለም፤አትሌቲክሱን ደምተንለታል፣ቆስለንለታል፣35 ዓመታት ታግለንለታል፤አሁንም ከ35 ዓመት በኃላም እየታገልንለት ነው፤ሁሉም እንዲያውቅልን የምንፈልገው እኛ ከማንም ጋር የግል ፀብ እንደሌለን ነው፤ስፖርቱን የማያውቁ ሠዎች አትሌቲክሱን ለምን ነኩብን ነው ችግሩ፤አንድ ነገር እወቅልን እዚህ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ያሉ ሠወሰች አንዳቸውም አትሌቲክሱን አያውቁትም ይሄን ቃል ስናገር በጣም አዝናለሁ፤ ምን አልባት ብርሃኔ አደሬ እዛ ኮሚቴ ውስጥ አለች እሷ ስለሩጫ፣ስለላብ፣ስለመድማት በተግባር ታውቃለች ሌሎቹ ግን አዝናለሁ አንዳቸውም አያውቁትም፤እንዳልኩህ ከማንም ጋር ችግር የለብንም፤ስፖርቱን፣አትሌቲክሳችንን ከሚነካ ጋር ግን ችግር አለብንና እባካችሁ ስፖርቱን ተወት አድርጉልንን፣ገለል በሉልን ነው የምለው…እኔ አርቲስት፣ሙዚቀኛ፣ሠዓሊ ነኝ ብዬ ወደሠው ሙያ አልመጣሁም፤ላለፉት 37 ዓመታት ለለፋሁለት፣ለደማሁለት አትሌቲክስ ግን ዛሬም እየታገልኩ ነው፤አትሌቲክሳችንን ልትተውልን ይገባል ነው የምለው።”

🎤…የመጨረሻ ቃልህ…

✍”…የሁለቱ ልዩነት በዚህ መልኩ መፈታቱ በጣም ነው ያስደሠተኝ፤ከእኔ በላይ ሠላም በመውረዱ ሲጨነቁ የነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሠዎች በመደሠታቸው የበለጠ ደስ ብሎኛል፤ይሄ ዕርቅ ዕውን እንዲሆን የደከሙትን ዋናውና ዕርቁ ዕውን እንዲሆን አባገዳዎችንና አባሙዳን፣አሠልጣኞችንና ታላላቅ ሠዎችን ያስተባበረውን ወንድማችንን ወርቁ ቢቂላን በጣም ነው የማመሠግነው፤የተከበሩ አባገዳ ጎበና ከኤሬቻ ጋር በተያያዘ ሌላ ፕረግራም ስለነበራቸው ባይገኙም ከአባሙዳ ጋር በጋራ በመሆን ደራርቱን ቤቷ ድረስ በመሄድ፣ገዛኸኝንም በማነጋገርና በመቆጣት ወደቀድሞ አንድነታቸው በመመለሳቸው ለሀገር፣ለአትሌቲክሱ ትልቅ ውለታን ውለዋልና በጣም ሊመሠገኑ ይገባል።

10 comments

Ecie Hab October 7, 2024 - 3:08 pm

በውስጥ መስመር ኑ አጠር አድርጌ ልንገራቹ 😂

Reply
ቻው ቼልሲ October 7, 2024 - 3:08 pm

በ ስናይፐር ላለመጠብጠብ የሚደረግ ጥረት 😂😂😂

Reply
Feysel Abrar October 7, 2024 - 3:10 pm

አሁን በፔንሲዮን ይጠባጠቡ😆

Reply
Kidist Tesfaye October 7, 2024 - 3:10 pm

እሰይ እግዚአብሔር ይመስገን እንኳን ታረቁ ፡፡ስናይፐሩ ግን ሁሌ ብቻዬን ስሆን ትዝ እያለኝ ያስፈግገኛል🤣

Reply
Mequanint Godo October 7, 2024 - 3:11 pm

እንደኔ ይሄን ፅሁፍ አንንብቦ #ያልጨረሠ እጅ ያውጣ!🤚

Reply
Teigistu Asefw October 7, 2024 - 3:12 pm

ደራርቱ ግን ይመችሽ አስበረገግሽው

Reply
Aeamy Diogan Jr. October 7, 2024 - 3:12 pm

ወይ ሰይጣን ስንቱን ቅሸባ ቻለኸው አንተን ባይሰጠው ይሄ ህዝብ ምን ይውጠው፡፡

Reply
Semi Tirago October 7, 2024 - 3:12 pm

Comment wusti siyatane eyayawu new

Reply
Dinaol Bulto Gedefa October 7, 2024 - 3:13 pm

Qoyi tetaltoo neberuu?

Reply
Hamona Selassia October 7, 2024 - 3:13 pm

ሁሉን ነገር በሰይጣን አሳባችሁ ትችሉታላችሁ

Reply

Leave a Comment