💒💒
#እጅግ አብዝቶ የሚገርመው ሞት
ለአዳም የተነገረው ቃል የማይፈጸምበት ሰብአዊ ፍጡር የለም፡፡ መሬትነትና ወደ መሬት መመለስ ኃያላን በጉልበታቸው፣ ነገስታት በሰራዊታቸው፣ ሌላው ቀርቶ አማላካችን እግዚአብሔር በቅድስናቸው ከፍ ያደረጋቸው ቅዱሳን ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃንና ሰማዕታት ሁሉ ስጋዊ ሞትን ቀምሰዋል፡፡ እነርሱ ግን በስጋዊ ሞታቸው ወደ ዘለዓለማዊ የክብር እረፍታቸው ነው የሔዱት፡፡ የሕይወትና የሞት ባለቤት እርሱን ወለደችው የቅድስት ድንግል ማርያም ሞት ግን ከሁሉ ይገርማል፡፡ የአምላክ እናቱ ስትሆን ሞትን ግን ቀምሳለች፡፡ ሞትስ ለሟች ይገባዋል የእመቤታችን የቅድስት ማርያም ሞት ግን አስደናቂ ነው፡፡
በምድር ላይ 64 ዓመት የኖረችው ቅድስት ድንግል ማርያም በአባት በእናቷ ቤት ሦስት ዓመት፤ በቤተ መቅደስ ዐሥራ ሁለት ዓመት፤ ከልጇ ጋር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወራት፤ ከጌታ ስቅለት በኋላ በመስቀል ላይ ሳለ አደራ በሰጠው፣ ጌታ በሚወደው ሐዋርያ፣ በወንጌላዊው በቅዱስ ዮሐንስ ዐሥራ አምስት ዓመታት ኖራለች፡፡ ጌታን የፀነሰችበትን ወራት ስንጨምር እመቤታችን በዚህ ዓለም በሥጋ የቆየችበት ጊዜ ስድሳ አራት ዓመት ይሆናል፡፡ ልጇ ወዳጇ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምታርፍበት ጊዜ እንደደረሰ ሲነግራት ሞትን መቅመስ እንደማትፈልግ ነገረችው፡፡ እርሱም ስጋን የለበሰ የአዳም ዘር ሁሉ ሞትን እንደሚያይ ነገራት፤ በመላእክት ምስጋና፣ በዳዊት ዝማሬ ቅድስት ነፍሷ ከቅድስት ስጋዋ ተለየች፡፡
የቅድስት ድንግል ማርያም ሞት በሁለት ምክንያት እንደሆነ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ያስረዳል፡፡ የመጀመሪያው “ዓለሙን ሁሉ ፈጥሮ ለሚገዛው ለመለኮት ማደሪያ ለመሆን የበቃችው ከሰማይ የመጣች ብትሆን ነው እንጂ የሰው ልጅስ አይደለችም፤” በማለት የሚነሱ መናፍቃን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የሰውን ባሕርይ አለበሰምና ያልተቀበልነው ለዚህ ነው እንዳይሉ ነው፡፡ ሞቷ ግን የሰው ልጅ እጣ ፈንታ የሆነውን ጽዋ እንድትቀበል አድርጓታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ሲያስረዳ ለዕብራውያን ሰዎች በላከው መልዕክቱ ዕብ 2÷14-15 “የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም›› አለ፡፡ በዚህም ድንግል ማርያም የአዳም ዘር መሆኗ ታወቀ፡፡
ሁለተኛው ጌታችን በፍርዱ አድልዎ የሌለበት አምላክ መኾኑ ይታወቅ ዘንድ ሥጋ የለበሰ ዅሉ በለበሰው ሥጋ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ግድ ነውና ቅድስት ድንግል ማርያም ሞትን ቀመሰች፡፡ ይህን ቅዱስ ያሬድም መስክሯል፡፡ በበዓለ አስተርዕዮ ጥር 21 ቀን ቅድስት ድንግል ማርያም በክብር አርፋለች፡፡ አስተርእዮ ማለት መታየት፣ መገለጥ ማለት ነው። ቃሉ አስተርአየ ታየ፣ ተገለጠ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በሥጋ የተገለጠበት የታየበት፣ አንድነት ሦስትነቱም የተገለጠበት ወቅት በመሆኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ በሙሉ ዘመነ አስተርእዮ በመባል ይታወቃል። የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ስለሚከበር “አስተርእዮ ማርያም” ተብሏል።
ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391
ወይም
አቢሲኒያ ባንክ
141029444
የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444
1 comment
ተረትተረት