#FastMereja | በኢትዮጵያ የግል የባንክ ኢንዱስትሪ ቀዳሚ የሆነው አዋሽ ባንክ፣ “ክብራችን ወገናችን – ደስታችን ማካፈላችን” በሚል መሪ ቃል የ2018 ዓ.ም የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ5ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ደጋፍ አደረገ።
ባንኩ ዛሬ ታህሳስ 23 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሳሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ባካሄደው መርሃ ግብር፣ አረጋውያን እና አቅመ-ደካማ ወገኖች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ የዓይነት እና የገንዘብ ድጋፍ አበርክቷል።
የድጋፉ ይዘት ለእያንዳንዱ ተጠቃሚ የተደረገው ድጋፍ በገንዘብ ሲሰላ ከ9,000 ብር በላይ ግምት ያለው ሲሆን፣ 25 ኪሎ ግራም ዱቄት፣ 5 ሊትር የምግብ ዘይት፣ 3,000 ብር ጥሬ ገንዘብ ሲሆን ባንኩ ለዚህ ሀገር አቀፍ የበጎ አድራጎት ተግባር በድምሩ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ገልጿል።
ማህበራዊ ኃላፊነት እና ሰው-ተኮር ተግባራት
አዋሽ ባንክ ላለፉት 31 ዓመታት በትምህርት፣ በጤና፣ በስራ ፈጠራ እና በአቅመ-ደካሞች ቤት ግንባታ ላይ በስፋት ሲሳተፍ ቆይቷል። ባንኩ ባለፈው የ2024/25 በጀት ዓመት ብቻ ለማህበራዊ ኃላፊነት አገልግሎቶች ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኑ ተገልጿል።
ከበዓላት ድጋፍ ባሻገር፣ ባንኩ በተለያዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች ፈጣን ድጋፍ በማድረግ እና በመንግስት የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን በማገዝ ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው።
አዋሽ ባንክ በቀጣይም የህዝብ ወገንተኝነቱን በተግባር ለማሳየት የጀመራቸውን ሰው-ተኮር ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመርሃ ግብሩ ላይ ተመላክቷል።




