#FastMereja I ማያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በአፈጣጠር ችግር ምክንያት የሚወለዱ ህፃናት ዙሪያ የግንዛቤ ማሰጨበጫ መርሀ-ግብር በዛሬዉ እለት ተካሂዷል።
በዛሬዉ ግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ ስለ ነርቭ ዘንግ አፈጣጠርችግር እና የጭንቅላት ውስጥ ፈሳሽ ከመጠን በላይ ክምችት ወይም “የስፖይና ቢፊዳ እና ሀይድሮሴፋለስ” በሽታ ምንነት እንዲሁም የበሽታውን መንስዔ እና መፍትሔ በባለሙያዎች የታገዘ ግንዛቤን ማስጨበጫ መርሀ ግብር ነዉ የተካሄደዉ፡፡
ስፓይና ቢፊዳ (የነርቭ ዘንግ አፈጣጠር ) ችግሮች ውስጥ አንዱ ሲሆን የአከርካሪ አጥንትና የህብለ ሰረሰር በአግባቡ አለመዘጋት/ክፍተት ነው፡፡
ሃይድሮሴፋለስ (የጭንቅላት ውስጥ ከመጠን በላይ የፈሳሽ ክምችት) ሲሆን ይህም የአዕምሮ ግፊት እንዲጨምርና የራስ ቅል ላይ መሰንጠቅን ሊያስከትል ይችላል።
በሃገራችን በአመት ከ44,000 እስከ 50,000 የሚሆኑ ህፃናት በዚሁ ችግር ምክንያት የሚፈጠሩ ሲሆን ዋነኛ ምክንያቱም የፎሊክ አሲድ ወይም የቫይታሚን ቢ9 እጥረት መሆኑም ተገልጿል ::
በመሆኑም እነዚህ ህፃናት በዚሁ ህመም ምክንያት ለእድሜ ልክ የመንቀሳቀስ ችግር እና እራሳቸውን ችለው የመፀዳዳት ችግር እንደሚገጥማቸዉ ነዉ የተገለፀዉ።
የፎሊክ አሲድ እጥረትን ለመከላከል እናቶች በመጀመሪያ የእርግዝና ወራቶች በእንክብል መልክ የሚሰጥ መድሃኒት መውሰድ እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን የአመጋገብ ስርአትንም ማስተካከል የፎሊክ አሲድ ችግርን ለመቅረፍ ወሳኝ ነው ተብሏል።
ከግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ-ግብሩ በተጨማሪ ማያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ለ74 የድርጅቱ አባላት የገና በአልን በማስመልከት ልዩ የማዕድ ማጋራት እንዲሁም የስጦታ መርሀ-ግብር ተከናዉኗል።




