banner

የአርሲ ሮቤ ነዋሪዎች የዘመናት የመሠረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ አገኘ

​#FastMereja I ከአዲስ አበባ በ215 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የአርሲ ዞን የሮቤ ወረዳ ዋና ከተማ ሮቤ፣ ለበርካታ ዓመታት የልማት ማነቆ ሆነውባት የቆዩት የመንገድና የመብራት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸው ተገለጸ። በተለይም ከኢተያ ተነስቶ ወደ ከተማዋ የሚዘልቀው የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ለነዋሪዎቹ ትልቅ ደስታን ፈጥሯል።

​አርሲ ሮቤ የንግድና የግብርና እንቅስቃሴ የሚታወቅባት ከተማ ብትሆንም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና የመንገድ መበላሸት ለከተማዋ እድገት ትልቅ እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ ነዋሪዎች ተስፋ በመቁረጥና አማራጭ ፍለጋ ወደ አዳማ፣ አሰላና ሌሎች ከተሞች በመሰደድ ላይ ነበሩ። አሁን ግን መሠረተ ልማቶቹ መሟላታቸው ከተማዋን ወደ ቀድሞ የንግድ መነቃቃት እንደሚያመጣታት ተስፋ ተጥሎበታል።

​ለበርካታ ጊዜያት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦለት ሳይሰራ የቆየው የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት፣ በመጨረሻም ከኢተያ ተነስቶ በ2018 ዓ.ም አርሲ ሮቤ ከተማ ደርሷል። መንገዱ መገንባቱ የትራንስፖርት እንግልትን ከመቀነሱም በላይ፣ የአካባቢው አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀላሉ ወደ ገበያ ለማቅረብ ያስችላቸዋል።

​የአካባቢው ነዋሪዎች በገለጹት አስተያየት፣ ምንም እንኳ የመንግስት መሠረተ ልማቶች ወደ አርሲ ዲደዓ ሮቤ አካባቢዎች ዘግይተው ቢደርሱም፣ አሁን የተገኘው ምላሽ ግን ለዘመናት ለነበረው ጥያቄ ትክክለኛ መፍትሔ መሆኑን ገልጸዋል።

​አሁን ከተማዋ ዘመናዊ መንገድ በመዘርጋቱ፣ የቀድሞ ነዋሪዎች ወደ ከተማዋ እንዲመለሱና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እንዲስፋፉ በር ይከፍታል ተብሏል።

“አርሲዎች እንኳን ደስ አላችሁ!”

Leave a Comment