#Fastmereja : ሞቲ ኢንጂነሪንግ ኃ.የተ.የግ.ማ. ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ስምንት ሕጻናትን ለማሳከም የ2 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን በዛሬው እለት ገልጿል።
በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ላለፉት 36 ዓመታት ከ9 ሺህ በላይ ለሆኑ ታካሚዎች የነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየ ሀገር በቀል ለትርፍ ያለተቋቋመ ተቋም ሲሆን ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚመጡ ሁሉን ያካተተ የልብ ሕክምና አገልግሎት ከክፍያ ነጻ በመስጠት ላይ የሚገኝ ተቋም መሆኑ ተገልጿል::
ማዕከሉ በሚሰጣቸው የነጻ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎቶች የሕጻናትን ጤና በመመለስ በሕጻናት ዕድገት እና ትምህርት ላይ አዎንታዊ አስተዋጾ ማበርከት ሲችል በዘርፉ የሰለጠኑ የጤና ባለሞያዎችን በማፍራትና ለልዩ ልዩ የትምህርት ማዕከላት እንደ መማሪያ መዳረሻ እያገለገለ ይገኛል።
ድርጅቱ ሁሉም የህክምና ወጪዎች ያለምንም ክፍያ በነፃ የሚያከናዉን ሲሆን አስፈላጊ ወጪዎችን ከማህብረተሰቡ በሚሰበሰብ ዕርዳታ፤ ከሀገር በቀል እና የዉጪ ድርጅቶች በሚደረግ ድጋፍ በመሸፈንም ቤተሰቦችን ከሥነ ልቦና ከማኅበራዊ እና ከኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን መታደግ መቻሉ ተገልጿል።
በዛሬው ዕለትም በኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ (ICT)፣ በኔትወርክ መሠረተ ልማት፣ በኢ-ግብይት ሂደት፣ በድርጅት ሶፍትዌር ልማት፤ በዲጂታላይዜሽን፣ በሲስተም ኢንተግሬሽን እና በATM አቅርቦት ዙሪያ አገልግሎት የሚሰጥ ኩባንያ የሆነው ሞቲ ኢንጂነሪንግ ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ድጋፍ አድርጓል።
ከዚህ በተጨማሪ በቀጣይነትም በየዓመቱ 4 ሕጻናትን ለማሳከም ለማዕከሉ የ አንድ ሚሊየን ብር ድጋፍ ለማድረግ ተስማምቷል።



