#Fastmereja:-በህዳር ወር የሚከበረው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን እና የዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብት ስምምነት 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተለያዩ መርሐ-ግብሮች ተከብሯል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግም ፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ብሔራዊ ማህበር በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ፣ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በህይወታቸው ዙሪያ በሚደረጉ ማናቸውም ውሳኔዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑና መብታቸው ሊከበር እንደሚገባ ገልፀዋል።
ማህበሩ በመግለጫው እንዳስታወቀው፣ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች ልክ እንደማንኛውም ሰው ህልም፣ ተሰጥኦና ምኞት ያላቸው በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በዓሉን “ያገባኛል፣ ይመለከተኛል” በሚል የባለቤትነት ስሜት እንዲያከብሩ ጠይቋል። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአካል ጉዳተኞች መብትና ተሳትፎ ረገድ መሻሻሎች ቢታዩም፣ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች አሁንም ከፍተኛ መገለል፣ መድልዎ እና አሉታዊ አመለካከቶች እንደሚያጋጥሟቸው ተገልጿል።
በተለይም ሁሉን አቀፍ ትምህርት፣ የሙያ ስልጠና፣ የሥራ ዕድል፣ የጤና አጠባበቅ እና የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎቶችን በማግኘት ረገድ አሁንም ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸውን ማህበሩ አመላክቷል።
እንደመሁም ብዙ ጊዜ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ዜጎች የሚመለከቱ ውሳኔዎች የሚተላለፉት ራሳቸውን ሳያማክሩና ሳያሳትፉ መሆኑ ችሎታቸውና አስተዋጽኦአቸው ችላ እንዲባልና ሙሉ አቅማቸውን እንዳይጠቀሙ እንቅፋት መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ “ስለ እነርሱ ምንም ነገር ያለ እነርሱ መወሰን የለበትም” ሲሉ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ በህብረተሰቡ ዘንድ ባለው የግንዛቤ እጥረት ምክንያት በርካታ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆችና ወጣቶች በቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው ለተደራራቢ ጉዳቶች እንደሚጋለጡም ማህበሩ አስታዉቆ ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት፣ የልማት አጋሮች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ እና ቤተሰቦች የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች በሁሉም የህይወት ዘርፎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ምቹ ማህበረሰብ ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያድሱ ማህበሩ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ጥሪ አቅርቧል።
ፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ብሔራዊ ማህበር በ1987 ዓ.ም የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ባለባቸው ልጆች ወላጆች የተቋቋመ ሀገር በቀል ድርጅት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በዘጠኝ የክልል ከተሞች ከ17 በላይ ቅርንጫፎችን በመክፈት ከቤት ተደብቀው የነበሩ ልጆችን በማውጣት የትምህርት፣ የጤና፣ የሥራ ዕድልና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ከ16,000 በላይ ለሚሆኑ አባላቱ ድጋፍና እንክብካቤ እየሰጠ ይገኛል።




