#FastMereja I አሜሪካ በኢራን ላይ በከፈተችው ወታደራዊ ጥቃት በመጀመሪያዎቹ 24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ 779 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ወጪ ማድረጓን የአናዶሉ የዜና ወኪል መረጃዎችን ጠቅሶ ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘገበ። ይህ ወጪ የአሜሪካ የ2026 መደበኛ የመከላከያ በጀት 0.1 በመቶ ያህሉ ነው።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፣ በዘመቻው ላይ እጅግ ዘመናዊ የሆኑት ቢ-2 ስውር ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች፣ ኤፍ-22 እና ኤፍ-35 ተዋጊ ጄቶች እንዲሁም ኤምኪው-9 ድሮኖች ተሳትፈዋል። በተጨማሪም በኒውክሌር ኃይል የሚሰሩ ግዙፍ የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች እና የፓትሪዮት ሚሳይል መከላከያ ስርአቶች በጥቃቱ ላይ ውለዋል።
አራት የቢ-2 ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ከአሜሪካ ሚዙሪ ግዛት ተነስተው ጥቃት ለማድረስ ብቻ 30.2 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎባቸዋል። እንደ ኤፍ-18 እና ኤፍ-35 ያሉ ተዋጊ ጄቶች ላከናወኑት ተልዕኮ ደግሞ 271.34 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሆኗል።
የድሮን ጥቃቶችን፣ የሰላዮች አውሮፕላኖችን እና የምድር ላይ የሂማርስ ሚሳይል ባትሪዎችን ጨምሮ ለተቀናጀው የአየርና የምድር ጥቃት የወጣው ወጪ 423.57 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል።
በቀጣናው የሚገኙት የዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን እና ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች ከነአጃቢዎቻቸው ጋር ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ በቀን 15 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እየጠየቀ ይገኛል።
ይህ ግዙፍ ወጪ የተሰላው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር የ2025 እና 2026 የበጀት ሰነዶችን፣ የአውሮፕላኖችን የበረራ ሰዓት እና የጥገና ወጪ እንዲሁም ጥቅም ላይ የዋሉትን የጦር መሳሪያዎች ዋጋ መነሻ በማድረግ እንደሆነ ተመልክቷል።
