#FastMereja I የሴኔጋል ፓርላማ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የግብረ-ሰዶማውያን ግንኙነቶችን የሚቀጣውን ከፍተኛ የእስራት ዘመን ከአምስት ዓመት ወደ 10 ዓመት ከፍ የሚያደርግ አዲስ ሕግ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
በግብረ-ሰዶማዊነት ድርጊት የተገኘ ማንኛውም ሰው ከዚህ ቀደም ይጣልበት የነበረው የ5 ዓመት እስራት አሁን እስከ 10 ዓመት ሊደርስ ይችላል።
ጥፋተኞች ከ3,500 እስከ 17,600 የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል። ሕጉ ድርጊቱን መፈጸምን ብቻ ሳይሆን፣ የግብረ-ሰዶማውያን ግንኙነቶችን ማስተዋወቅ ወይም በገንዘብ መርዳትንም የወንጀል ድርጊት አድርጎታል። ለዚህም ከ3 እስከ 7 ዓመት የሚደርስ እስራት ይደነግጋል።
ድርጊቱ ለአቅመ-አዳም ያልደረሱ ህፃናትን የሚያካትት ከሆነ ከፍተኛው የቅጣት እርምጃ ተፈጻሚ ይሆናል።
አዲሱ ሕግ ያለበቂ ማስረጃ ሰዎችን በግብረ-ሰዶማዊነት በሀሰት የሚወነጅሉ ግለሰቦችንም በወንጀል የሚያስቀጣ አንቀጽ አካቷል።
ይህ ረቂቅ ሕግ በፓርላማው 135 ለ 0 በሆነ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን፣ ሦስት ተወካዮች ደግሞ ድምፅ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ሕጉ በጠቅላይ ሚኒስትር ኡስማን ሶንኮ አቅራቢነት ለፓርላማው የቀረበ ሲሆን፣ አሁን ተግባራዊ ለመሆን የፕሬዝዳንት ባሲሩ ዲዮማይ ፋዬን ፊርማ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
