#FastMereja I ጋሞ
የክራይስት አርሚ ኢንተርናሽናል ቤተክርስቲያን መስራች ነብይ እዩ ጩፋ በጋሞ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ማቋቋሚያ የሚሆን የ300 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል። በዞኑ አራት ወረዳዎች በተከሰተው በዚህ አሰቃቂ የተፈጥሮ አደጋ የ81 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተረጋግጧል።
በድጋፍ ርክክቡ ወቅት ነብይ እዩ ጩፋ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸው፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል። ነብዩ አክለውም አደጋው የበርካታ ደጋግ ወገኖችን ህይወት የቀጠፈ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተረፉትን በዘላቂነት ለማቋቋም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እጁን እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም መሰል አደጋዎች እንዳይደገሙ የሃይማኖት ተቋማት ጸሎት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ደምሴ አድማሱ በበኩላቸው፣ ቤተክርስቲያኗ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላደረገችው የገንዘብና የሞራል ድጋፍ በመንግስትና በተጎጂዎች ስም ምስጋና አቅርበዋል። እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ህብረተሰቡን ያስተባበረ ሰፊ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
የጋሞ ዞን ኮሙኒኬሽን እንደዘገበው፣ የተደረገው የ300 ሺህ ብር ድጋፍ ለመጀመሪያ ዙር ማቋቋሚያ የሚውል ሲሆን፣ ቀጣይ ድጋፎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል።
