banner

እስራኤል ኢራን በሕፃናት ላይ “ደመ ነፍሳዊ ጥቃት” እያደረሰች ነው ስትል ለዩኒሴፍ ክስ አቀረበች

​#FastMereja I የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢራን መንግስት በእስራኤል ሲቪሎች በተለይም በሕፃናት ላይ የሚፈጽመውን የባሊስቲክ ሚሳኤል ጥቃት የዓለም አቀፉ የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) በጽኑ እንዲያወግዝ ጠየቀ። ሚኒስቴሩ በላከው ይፋዊ ደብዳቤ ኢራን በሕዝብ በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የታገዱ “ክላስተር ቦምቦችን” እየተጠቀመች መሆኑን ገልጿል።

​በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኒና ቤን-አሚ ለዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራሰል በላኩት ደብዳቤ ላይ የተጠቀሱ ዋና ዋና ነጥቦች፦

​መጋቢት 21 (እ.ኤ.አ) በሪሾን ሌጽዮን (Rishon LeZion) ከተማ 11 የተለያዩ ቦታዎች ላይ የኢራን ክላስተር ሚሳኤሎች ያረፉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የአጸደ ሕፃናትና የሕፃናት ማቆያ ማዕከላት ይገኙበታል።

​በዚሁ ዕለት በደረሰ ሌላ ጥቃት 115 ሲቪሎች ወደ ሶሮካ የሕክምና ማዕከል የተወሰዱ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 18ቱ ሕፃናትና ጨቅላዎች ናቸው። አንዲት የ5 ዓመት ሕፃን በጽኑ ሕክምና ላይ ስትሆን፣ ሌሎች አራት ሕፃናትም በሕይወትና በሞት መካከል እንደሚገኙ ተገልጿል።

በዲሞና ከተማ በደረሰ ጥቃት የመኖሪያ ሕንፃ በከፊል መፈራረሱና የ10 እና 12 ዓመት ታዳጊዎችን ጨምሮ 60 ሰዎች መቁሰላቸው ተጠቁሟል።

​ከመጋቢት 1 ጀምሮ በቤት ሸመሽ፣ ቢርሸባ እና ኤይላት በደረሱ ጥቃቶች የሦስት እህትማማቾችን ሕይወት ጨምሮ በርካታ ሕፃናት መገደላቸውና መቁሰላቸው በደብዳቤው ተዘርዝሯል።

​በሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ሕፃናት በሚሳኤል ፍንዳታና ለረጅም ሰዓታት በቦምብ መጠለያዎች ውስጥ በመቆየታቸው ምክንያት ለከፍተኛ ጭንቀትና ስነ-ልቦናዊ ቀውስ መዳረጋቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

​እስራኤል ዩኒሴፍ ይህንን የኢራን “ጭካኔ የተሞላበት” ድርጊት በአስቸኳይና በግልጽ እንዲያወግዝ እንዲሁም ለእስራኤላውያን ሕፃናት መብት እንዲቆም ጥሪ አቅርባለች።

Leave a Comment