#FastMereja I አዲስ አበባ
ታዋቂው ድምፃዊ አቤል ሙሉጌታ ከዓለማዊ የዘፈን ህይወት ሙሉ በሙሉ በመውጣት ወደ መንፈሳዊ አገልግሎት መመለሱን በይፋ አስታወቀ። ድምፃዊው ይህንን ውሳኔ ያስታወቀው “ከእንግዲህ በዘፈኑ ዓለም የለሁም” በሚል ጠንከር ባለ መልዕክት ነው።
ባለፉት ዓመታት በዘፈን ስራዎቹ የሚታወቀው አቤል፣ የዘፈን ዓለም “ውስብስብና አጋንንታዊ አሰራር ያለበት” መሆኑን በመጥቀስ፣ በተደጋጋሚ ወደ መንፈሳዊ ህይወት ለመመለስ ቢሞክርም ሳይሳካለት መቆየቱን ገልጿል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ “የጠፋው ልጅ ተገኝቷል” በማለት ዳግም ወደ ቀድሞ እምነቱ መመለሱን አረጋግጧል።
አቤል የዘፈን ዓለምን “ቆሻሻ፣ ውሸትና ከንቱ” ሲል የገለጸው ሲሆን፣ በተለይም የዘፋኝነት ህይወት ከስካር ጋር የተቆራኘ መሆኑን ጠቁሟል::
ከ2005 እስከ 2007 ዓ.ም ለሁለት ዓመታት ያህል ዘፈን አቁሞ እንደነበረና በኋላ ግን ተመልሶ እንደገባ አስታውሷል።
ለዘማሪ በረከት አለሙ የሰጠውና በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው “እሰይ” የተሰኘው ዝማሬ፣ ገና በ2003 ዓ.ም “በጨለማው ዓለም” ሆኖ የአባቱን (የፈጣሪን) ቤት ናፍቆ የጻፈው እንደነበር ገልጿል።
ድምፃዊው ከእንግዲህ ወደ ዘፈን ዓለም እንደማይመለስና ህይወቱን ለፈጣሪ አገልግሎት መስጠቱን ገልጾ፣ በዘፈን ዓለም ያሉ ጓደኞቹም የእሱን ፈለግ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርቧል።
