banner

“1.5 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ዓለም አቀፍ ኮንሰርት ነው የማዘጋጀው” ድምፃዊት ቬሮኒ

“1.5 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ዓለም አቀፍ ኮንሰርት ነው የማዘጋጀው” ድምፃዊት ቬሮኒካ አዳነ
​
#FastMereja I ​ድምፃዊት ቬሮኒካ አዳነ የ«መጠሪያዬ» አልበሟ ከተለቀቀ ከሦስት ዓመታት በኋላ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ታላቅ ዓለም አቀፍ ኮንሰርት ለማዘጋጀት ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቋን አስታወቀች።

አርቲስቷ ዛሬ ጥቅምት 11 ቀን 2019 ዓ.ም በራማዳ ሆቴል በሰጠችው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀችው፣ እስካሁን በፕሮሞተሮች የቀረቡትን ጥያቄዎች ሳትቀበል ቆይታ፣ አሁን በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ የሙዚቃ ዝግጅት ለማቅረብ መወሰኗን ነው የገለጸችው።

ይህንን ህልሟን እውን ለማድረግም ቤቷን በማስያዝ ከባንክ ብድር በመውሰድ ለዝግጅቱ የገንዘብ ምንጭ እንዳደረገችው በመግለጫው ላይ ተናግራለች። «ፕሮግራሙ እውን ሆኖ ኪሳራ ቢያጋጥመኝም ምንም አይመስለኝም፤ ቤቱን ሠርቼ የገዛሁት በመሆኑ፣ መልሼ ለሥራው እንዳዋልኩት ነው የማስበው» ብላለች።

​በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ይህ ኮንሰርት፣ በከፍተኛ የድምፅ፣ የብርሃንና የመድረክ ጥራት የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል። ዝግጅቱን ለማሳካትና አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ከታዋቂ የውጪ ሀገር ባለሙያዎች ጋር ጥምረት የተፈጠረ ሲሆን፤ በአፍሪካና ዓለም አቀፍ መድረኮች በሙዚቃ ሥራቸው ተቀባይነት ያተረፉ የውጪ ሀገር አርቲስቶችም የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡበት ተመላክቷል።

​ለኮንሰርቱ ስኬት ከአገር ውስጥ እና ከውጪ ሀገር የተውጣጡ ባለሙያዎች የተሰለፉ ሲሆን፤ ናይጄሪያዊቷ ቪክቶሪያ ንኮንግ የዝግጅቱ ተባባሪ አዘጋጅ በመሆን እየሰራች ትገኛለች። ናይጄሪያዊው ሴጉን ሶሎሞን የፕሮጀክት ማናጀር በመሆን፣ ፒተር ጊዴዎን ደግሞ የድምፅ፣ የምስል እና የቴክኒክ ክፍሎችን በኃላፊነት በመምራት ላይ ይገኛሉ።

ለዚህ ታላቅ ዝግጅት 1.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት የተያዘ ሲሆን፣ በኮንሰርቱ ላይ በነፃ የሚሳተፉ ታዋቂ የውጪ ሀገር ድምፃውያን የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ፓቶራንኪንግ፣ ዲጄ ኔፕቱን፣ ስቶንቦይ እና ራይቫኒ ይገኙበታል።

ዝግጅቱን የሚያስተባብረው «ሞሪያድ ኢቨንትስ» ዋና ስራ አስፈፃሚና የድምፃዊቷ ረዳት ማናጀር የሆነው ሞገስ መኮንን ከባለሙያዎቹ ጋር በመሆን ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ተናግሯል።

​በአዲስ አበባ ከተማ ታላቅ ድምቀት ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ታላቅ የ«መጠሪያዬ» ኮንሰርት ጥር 15 ቀን 2019 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።

#ኹነት





Leave a Comment